የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት፤ ለሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ለማምጣት በቅን ልቦና እንዲደራደሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት ይፋ ያደረጉትን እና በታንዛኒያ የሚደረገውን ድርድር፤ አሜሪካ በበጎ እንደምትቀበለው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
አንቶኒ ብሊንከን ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ለተጀመረው ድርድር ድጋፋቸውን የገለጹት፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት የተፈረመበትን ስድስተኛ ወር በማስመልከት ትላንት ማክሰኞ ሚያዝያ 24፤ 2015 ምሽት ባወጡት መግለጫ ነው። ብሊንከን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመው ስምምነት “ስኬት”፤ በኦሮሚያ ክልል “ሰላም ለማምጣት ያለውን ዕድል ይጠቁማል” የሚል እምነት አላቸው።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትላንቱ መግለጫቸው፤ የፕሪቶሪያውን ስምምነት “ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያን ግጭት አቁሞ ዛሬ የቀጠለውን የሰላም እና የማገገም ሂደት ያስጀመረ” ሲሉ ገልጸውታል። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም ከፍ ያለግፊት ሲያደርጉ ከቆዩ ጉምቱ ዲፕሎማቶች አንዱ የሆኑት የአውሮፓ ህብረት የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል፤ ከብሊንከን ጋር ባለፈው ወር በብራስልስ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በሰጡት መግለጫ የስምምነቱ መፈረም “በዓለም ላይ ካሉ ጥቂት በጎ ዜናዎች አንዱ” ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኩል ይፋ በሆነው በትላንቱ መግለጫ፤ በስምምነቱ ተገኝተዋል የተባሉ ትሩፋቶች ተዘረዝረዋል። ስምምነቱ “የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች ስራ እንዲጀምሩ፣ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ ህወሓት ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያስረክብ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ አስችሏል” ብለዋል ብሊንከን።
ሁሉን አቀፍ እና አካታች የሽግግር ፍትህ ጅማሮ እንዲሁም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረት፤ ብሊንከን የጠቀሷቸው ሌሎች የፕሪቶሪያ ስምምነት ውጤቶች ናቸው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ጉልህ እርምጃ” ሲሉ ለጠቀሷቸው ለእነዚህ ተግባራት እውን መሆን፤ የስምምነቱ ፈራሚ የሆኑት የፌደራል መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ላከናወኗቸው ስራዎች አድናቆታቸውን ቸረዋል።
ብሊንከን በመግለጫቸው፤ የስምምነቱ ትግበራ ይቀጥል ዘንድ መከናወን የሚገባቸው ጉዳዮችንም ጠቁመዋል። ተጨማሪ የሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ተቆጣጣሪዎች ማሰማራት እና ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ አደረጃጀቶቻቸውን የመበተን እና መልሶ ከማህበረሰቡ የማዋሃድ ሂደቱን በውጤታማ መንገድ ተግባራዊ በማድረግ የስምምነቱ ትግበራ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጫ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማውረድ “ቁልፍ ናቸው” ያሏቸውን ጉዳዮችንም በመግለጫቸው አንስተዋል። ከእነዚህ ውስጥ በቀዳሚነት የተነሳው የኤርትራ ወታደሮች እና የፌደራል ያልሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል “ሙሉ በሙሉ ለቀው መውጣት” የሚለው ነው። የሰብዓዊ መብቶች መብቶች “ጥሰቶችን እና በደሎችን የፈጸሙ” አካላትን ተጠያቂ ማድረግ የሚለው ደግሞ በተከታይነት ተጠቅሷል። “ተዓማኒ የሽግግር ፍትህን” ገቢራዊ ማድርግ የሚለው ሰላም ለማስፈን “ቁልፍ” ከተባሉ ጉዳዮች ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)