በአማኑኤል ይልቃል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚላኩለትን የምክክር አጀንዳዎች ከዛሬ ጀምሮ መቀበል እንደጀመረ አስታወቀ። ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን የመለየት ስራን፤ በአራት ክልሎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደሚያከናውንም ገልጿል።
የምክክር ኮሚሽኑ ዛሬ አርብ ግንቦት 11፤ 2015 በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ የሚጀመረው በጋምቤላ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሀረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንደሆነ ይፋ አድርጓል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ በአራቱ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባሉ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ “የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎች” “ይወክሉኛል” የሚሏቸውን ተሳታፊዎች እንዲመርጡ እንደሚደረግ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ተወካይ ያስመርጣሉ ተብለው ከተለዩት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል፤ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን እና የማህበረሰብ መሪዎች እንደሚገኙበት በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። የተገለሉ ህብረተሰብ ክፍሎች፣ እድሮች እና የንግድ ማህበረሰብም በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት መካከል ናቸው። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችም፤ “በባለድርሻ አካልነት” እንደሚቆጠሩ ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች እያንዳንዳቸው በየወረዳቸው 50 ተወካዮችን ከመረጡ በኋላ፤ ለልየታ ወደ የዞን ማዕከላት እንደሚልኩ ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል። በዚህ ሂደት የሚለዩት ተወካዮች በዞኖች ላይ በሚኖራቸው ቆይታ፤ ስልጠና እንደሚሰጣቸው እና “አጀንዳ ነው” ብለው በሚያስቡት ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ወደ ዞን ከመጡት የእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ውስጥ ሁለት ሰዎች እንደሚመረጡም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ገልጸዋል። በክልል ደረጃ በሚካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ የሚሳተፉት፤ እነዚህ ሁለት ተወካዮች መሆናቸውንም አክለዋል። በክልል ደረጃ የሚሰበሰቡት ተወካዮች፤ በየወከሉት ህብረተሰብ ክፍል ተከፋፍለው “ኮከስ” እንደሚፈጥሩ የገለጹት ሂሩት፤ ኮከሶቹ “የወከልነው የህብረተሰብ ክፍል ዋነኛ ጉዳዮች እነዚህ ናቸው” በማለት የለዩዋቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ እንደሚያቀርቡም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ የሚያከናውነው፤ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በሚከፍታቸው ቅርንጫፎች እንደሆነ ፕሮፌሰር መስፍን በዛሬው መግለጫ ላይ አስታውቀዋል። “ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሲቪክ ማህበራት፣ በምናገኛቸው በሌሎች ተቋማትም ልንጠቀም እንደምንችል ከአሁን በፊት በሰራናቸው ስራዎች አረጋግጠናል” ሲሉም ከዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪነት ኮሚሽኑ ቅርንጫፉን ስለሚከፍትባቸው ቦታዎች ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች መረጣውን በሚቀጥለው ሳምንት ሲጀምር፤ ሂደቱን ለመከታተል አስራ አንዱም ኮሚሽነሮች ወደ አራቱ ክልሎቹ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንደሚሰማሩ ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ኮሚሽነሮቹ በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች “የሂደቱን ተአማኒነት” የማረጋጋጥ ስራ እንደሚያከናውኑም አስረድተዋል። ሂደቱን በመታዘብ ረገድ፣ የምክክር ኮሚሽኑ “በተሳታፊ ልየታ ስራ ላይ እገዛ ያደርጉልኛል” ብሎ የለያቸው ስምንት “ተባባሪ” አካላትም ይሳተፋሉ ተብሏል።
በእያንዳንዱ ወረዳ አንድ አባል በመመደብ ሂደቱን ከሚታዘቡ ተባባሪ አካላት ውስጥ፤ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የመምህራን ማህበር ይገኙበታል። የአካባቢው “የዓውድ ጎሳ መሪዎች”፣ ሀገር አቀፍ የእድሮች ማህበራት ጥምረት እና የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤም እንደዚሁ ታዛቢ በሚመድቡ ተባባሪ አካላት ዝርዝር ውስጥ ተጠቅሰዋል። የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የወረዳ አስተዳደር ተወካዮችም ሂደቱን በመታዘብ እንደሚሳተፉ በዛሬው መግለጫ ተነግሯል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፤ ከተሳታፊዎች የመለየት ስራ ጎን ለጎን በቀጣዩ ሳምንት በዋናነት የሚያከናውነው ስራ “አጀንዳዎች ማሰባሰብ” መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ሊቀርቡ ይገባሉ የሚባሉ አጀንዳዎች “በቀጥታ ከህዝቡ” የሚሰበሰቡ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን አስታውሰዋል። በየክልሉ ከሚመጡ ተወካዮች ከሚቀርቡ አጀንዳዎች በተጨማሪ፤ ኮሚሽኑ ሌሎች “የተለያዩ አካሄዶችን” በመጠቀም አጀንዳዎችን እንደሚቀበልም ጠቁመዋል።
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ፣ የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ሁሉ፣ ‘እጅግ መሰረታዊ የሆነ አጀንዳ አለኝ’ የሚል ሁሉ፤ አጀንዳውን ወደ ኮሚሽኑ የመላክ መብት ይኖረዋል” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች “በኢሜል፣ በአካል ወደ ኮሚሽኑ በመምጣት እና በፖስታ” አጀንዳዎችን ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። ኮሚሽኑ በእንደዚህ አይነት መልኩ የሚመጡ አጀንዳዎችን ከዛሬ ጀምሮ መቀበል እንደሚጀምር ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ሂሩት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን የምክክር ኮሚሽኑ በምን ያህል ጊዜ አጀንዳ አሰባስቦ ለመጨረስ ያህል እንዳቀደ ሲያስረዱ፤ “እጅግ በጣም ተስፋ የምናደርገው በዚህ በጀት ዓመት በአጠቃላይ አጀንዳዎች ተሰባስበው፤ አዋጁ በሚያዘው መሰረት ከመላው ኢትዮጵያ እና በውጪ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን በኩል ተሰባስበው፤ ወደዚህ ምክር ቤት መጥተው ለልየታ ይቀርባሉ ማለት ነው” ብለዋል። ምክትል ኮሚሽነሯ ሂሩት በበኩላቸው “የሰበሰብነውን [አጀንዳ] ወስደን፣ analyze አድርገን፣ ሀገርን ሊያነጋግሩ የሚችሉ ‘በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው’ የሚለውን ከዚህ ውስጥ እናወጣለን” ሲሉ ቀጣይ የሚሆነውን ሂደት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህንን ሂደት የሚያከናውነው፤ ከቀናት በፊት ይፋ ባደረገው የአማካሪ ኮሚቴ እገዛ መሆኑንም ጠቁመዋል። የምክክር ኮሚሽኑ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ባወጣው መረጃ፤ የአማካሪ ኮሚቴው 35 አባላት እንዳሉት አስታውቆ ነበር። የአማካሪ ኮሚቴው አባላት “ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ በምክክር ሂደት ላይ ስራዎችን ካከናወኑ ግለሰቦች እና ከተቋማት ተወካዮች” የተወጣጡ መሆናቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)