በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተለቀቀ  

ዛሬ ቅዳሜ ምሽት ከመኖሪያ ቤቱ በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ የተወሰደው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ምሽት አምስት ሰዓት ገደማ መለቀቁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገረ። ተመስገን ለ“ጥያቄ ትፈለጋለህ” በሚል፤ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተወስዶ ለሁለት ሰዓት ገደማ መቆየቱን ገልጿል።

ተመስገን ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ነጻ በተባለበት ክስ ጋር በተያያዘ፤ ይግባኝ እንደተጠየቀበት ዛሬ ምሽት በፖሊስ እንደተገለጸለት አስረድቷል። በዚህ ክስ ይግባኝ የቀረበለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዝገቡን በሚያዝያ 12፤ 2015 ዘግቶት እንደነበር ተመስገን አስታውሷል። ይህም ሆኖ ጉዳዩ እንደገና በጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚታይ በፖሊስ እንደተነገረው ተመስገን አክሏል። 

ለዚህም ሲባል ሰኞ በአካል የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲቀርብ መጠየቁን እና ይህንኑ የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ላይ መፈረሙንም ጋዜጠኛው አስታውቋል። ከዚህ ሂደት በኋላ የመታወቂያ ዋስ በማስያዝ ከሁለት ሰዓት እስር በኋላ መለቀቁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በኩል የሚገኘውን መረጃ አካትተን፤ ዝርዝር ዘገባ ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን።

ጋዜጠኛ ተመስገን ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 12፤ 2015 ምሽት በአዲስ አበባ ጃንሜዳ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ የተወሰደው በሁለት ፒክ አፕ ተጭነው በነበሩ እና የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች መሆኑን የዓይን እማኞች ቀደም ብለው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀው ነበር። እስከ ምሽት ድረስ ከቅርብ ጓደኞቹ ጋር የነበረው ተመስገን፤ ወደ መኖሪያ ቤቱ በሚገባበት ወቅት የግቢ ዙሪያው በጸጥታ ኃይሎች ተከብቦ ማግኘቱን የዓይን እማኞቹ ተናግረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)