በኢትዮጵያ ካሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ “ከፍተኛ” የሚባለውን ደረጃ ያሟሉ፤ አራት ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ 

በአማኑኤል ይልቃል

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ካሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተፈላጊውን “ከፍተኛ ደረጃ” የሚያሟሉት አራቱ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ወላጆች፣ የቀድሞ ተማሪዎች እና መምህራንን የሚያሳትፍ፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ያለመ ሀገር አቀፍ የትምህርት ዘመቻ በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። 

የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 15፤ 2015 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ነው። ሪፖርቱን ለፓርላማ አባላት ያቀረቡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአጽንኦት ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፤ የትምህርት ቤቶችን ጥራት የሚመለከት ነው።

እርሳቸው የሚመሩት መስሪያ ቤት በሀገሪቱ አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ባሉ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግምገማ ማድረጉን የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በተገኘው ውጤት ላይ ተመስርቶ ትምህርት ቤቶቹ በአራት ደረጃዎች እንደተመደቡ ገልጸዋል። ግምገማው የተደረገው፤ ትምህርት ቤቶች በሚጠቀሟቸው ግብዓቶች፣ በመማር ማስተማር ሂደቶቻቸው እንዲሁም ተማሪዎቻቸው በሚያስመዘግቧቸው ውጤቶች ላይ እንደነበር አመልክተዋል። 

በዚህም መሰረት ግምገማ ከተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል “ከፍተኛ” የተባለውን “ደረጃ አራት” ያገኙት፤ አራት ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። የሚፈለገውን ደረጃ ያሟሉት በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ካሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያላቸው ድርሻ  0.001 በመቶ መሆኑን የጠቀሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ ሌሎቹ ትምህርት ቤቶች “የተጠበቀውን ደረጃ ያላሟሉ” መሆናቸውን ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል።

በዚሁ ግምገማ በተገኘው ውጤት፤ ከአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 85.9 በመቶ የሚሆኑት “ፍጹም ከደረጃ በታች” መሆናቸው መረጋገጡን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ደግሞ 70.9 በመቶ የሚሆኑትም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሚጠበቀው “ደረጃ በታች” ማስመዘገባቸውን አክለዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች፤ በግምገማው በ“ደረጃ አንድ” እና “ደረጃ ሁለት” ምድብ የተቀመጡ መሆናቸውንም አብራርተዋል። 

ትምህርት ሚኒስቴር የእነዚህ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ እና ጥራት ለማሻሻል፤ “ህብረተሰቡን በማስተባበር” ጥገና እና እድሳት እያደረገ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። በዚህ አይነት መልኩ 8,700 ገደማ ትምህርት ቤቶች ጥገና እና እድሳት እንደተደረገላቸውም በማሳያነት ጠቅሰዋል። ሚኒስትሩ ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ፤ በመስሪያ ቤታቸው የተደረገ ሌላ ጥናትንም በማሳያነት አንስተው ለፓርላማ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

ከዚህ ቀደም በነበሩ ፈተናዎች ተማሪዎች ያገኟቸው ውጤቶችን የዳሰሰው ይህ “የትምህርት ምዘና ጥናት”፤ ዘንድሮ በአራተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ መካሄዱ ተገልጿል። በዚህም መሰረት ፈተናዎችን ከወሰዱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ፤ ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡት 12 በመቶው ብቻ እንደሆኑ ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስታውቀዋል። ከአራተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ደግሞ ከግማሽ በላይ ያመጡት 20 በመቶው እንደሆኑ አስረድተዋል።

በጥናቱ የተደረሰባቸውን ውጤቶች በተመለከተ፤ በተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኩል ጥያቄ ቀርቧል። የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄዎች በንባብ ያቀረቡት አቶ ፍሬው ተስፋዬ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ “ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት ከመተንተን ባለፈ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ ያልቻለው ለምንድነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። 

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ “ተበላሽቷል” ያሉትን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ጊዜ እንደሚወስድ ተናግረዋል። “የእዚህን ሀገር የትምህርት ስርዓት በአንድ ዓመት እና በሁለት ዓመት የምንጨርሰው ቢሆን እና የምናሻሽለው ቢሆንማ በጣም በጣም ትልቅ ነገር ነው” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ መስሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ያላቸው “ሪፎርሞች” በአንድ ጊዜ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ መጠበቅ እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

በትምህርት ጥራት ላይ ተጽዕኖ ያላቸው ጉዳዮች በሚል ሚኒስትሩ በምላሻቸው የጠቀሱት፤ “የትምህርት ግብአት በበቂ አለመኖር” እንዲሁም “የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ጥሩ አለመሆን” ነው። “47 ሺህ ትምህርት ቤቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ወደ 99 በመቶ የሚሆኑት፤ ለተማሪዎች፣ ለልጆች አመቺ ሁኔታ የላቸውም” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በመንግስት በጀት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ጉድለቶችን ለማሟላት “ብዙ ጊዜ ይፈጃል” ብለዋል። 

ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴር “አጠቃላይ ማህበረሰቡን” የሚያሳትፍ “ሰፊ ዘመቻ” ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በኃላፊነት ይሳተፉበታል” በተባለው በዚህ ዘመቻ፤ ወላጆች፣ የቀድሞ ተማሪዎች እና መምህራን የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በዚህ ዘመቻ ተማሪዎች ጭምር “በጉልበት” እንደሚሳተፉም አክለዋል። 

ትምህርት ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ውስጥ ያለው ጉድለት ምን እንደሆነ “በዲጂታል ቴክኖሎጂ” በመታገዝ መረጃዎችን እያደራጀ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ይህንኑ ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። የትምህርት ቤቶችን ጥራት እና ደረጃ የማሻሻል ስራ በአምስት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች የማዳረስ ዓላማ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የትምህርት ቤቶችን የመማር ማስተማር ስራ ለማሻሻል በትምህርት ሚኒስቴር ትኩረት የተደረገበት ሌላኛው ጉዳይ፤ ለትምህርት ባለሙያዎች የሚሰጥ ስልጠና መሆኑ በዛሬው የፓርላማ ውሎ ተነስቷል። ሚኒስትሩ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ “በአዲሱ የትምህርት እርከን” መሰረት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ የሚያስፈልገውን ሰርተፊኬት ያሟሉ መምህራን ብዛት 80 በመቶ ነው። 

ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት የሚያስፈልገውን ዲፕሎማ የያዙ መምህራን 88 በመቶ ሲሆኑ፤ በሁለተኛ ደረጃ ለሚሰጥ ትምህርት በቂ የሆነውን ዲግሪ የያዙ መምህራን ደግሞ 94 በመቶ እንደሆኑ በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል። “መካከለኛ ደረጃ” የሚል ምድብ ያለውን የሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍሎች ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ዲግሪ ያላቸው መምህራን ብዛት ግን 18 በመቶ ብቻ እንደሆነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። ይህ ቁጥር በመካከለኛ ደረጃ ለማስተማር “ብቁ ያልሆኑ በርካታ መምህራን መኖራቸውን የሚያመላክት ነው” ብለዋል። 

የትምህርት ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በአጠቃላይ ለ12,500 ገደማ መምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የትምህርት አመራሮች ስልጠና መስጠቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሶስት ሺህ ገደማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራንም የአንድ ዓመት “ልዩ የስራ ላይ ስልጠና” መውሰዳቸውንም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)