በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በተቀሰቀሰ ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ  

በአማኑኤል ይልቃል

በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች ነዋሪዎች መካከል በተከሰተ ግጭት አምስት ሰዎች መገደላቸውን የልዩ ወረዳው አስተዳደር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታወቀ። በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰባት ሰዎች ደግሞ በህክምና ላይ መሆናቸውን አስተዳደሩ ገልጿል። 

የኑዌር፣ አኝዋ እና ኮሞ ብሔረሰቦች መኖሪያ በሆነው ኢታንግ ልዩ ወረዳ ግጭት የተቀሰቀሰው፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ግንቦት 13፤ 2015 መሆኑን የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡቦንግ ጊሎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚሁ ዕለት ጠዋት ጀልባ በመቅዘፍ ላይ የነበረ አንድ የሚሊሺያ አባል በጥይት ተመትቶ መገደሉ፤ በልዩ ወረዳው ለተነሳው ግጭት መነሻ ምክንያት  መሆኑንም አስረድተዋል።

ጥቃት የተፈጸመበትን የሚሊሺያ አባል ሁኔታ ለመመልከት ወደ ስፍራው የሄዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ተኩስ ከተከፈተ በኋላ ሁኔታው ወደ ግጭት ማምራቱን አቶ ኡቦንግ ገልጸዋል። ተኩሱን የከፈቱት “ደፈጣ ላይ” የነበሩ ታጣቂዎች መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይህን ጥቃት ተከትሎ የአኝዋ እና ኑዌር ብሔረሰቦች መኖሪያ በሆኑ ቀበሌዎች መካከል “ውጊያ” መጀመሩን አብራርተዋል።

በቀበሌዎቹ ነዋሪዎች መካከል እሁድ አምስት ሰዓት ገደማ አካባቢ የተጀመረው የተኩስ ልውውጥ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ተኩል ድረስ መቆየቱን የኢታንግ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ተናግረዋል። በዚህ ግጭት ሳቢያ በልዩ ወረዳው በሚገኙ የአራት የአኝዋ ቀበሌዎች ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቅቀው መሸሻቸውን አክለዋል። እነዚህ ነዋሪዎች ለቅቀዋቸው የሄዱ መኖሪያ ቤቶች፤ በግጭቱ ተሳታፊ በሆኑ ሰዎች ከትላንት በስቲያ ሰኞ መቃጠላቸውን አስረድተዋል። 

በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተነሳው በዚህ ግጭት፤ የሁለቱ ብሔረሰቦች ተወላጆች የሆኑ አምስት ሰዎች መገደላቸው እና ሰባት ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው አቶ ኡቦንግ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ጉዳት የደረሰባቸው የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች፤ ለህክምና በጋምቤላ ከተማ ወደሚገኘው ጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ለተሻለ ህክምና በጅማ ከተማ ወደሚገኝ ሆስፒታል እንዲዘዋወር መደረጉን ጠቁመዋል።

በልዩ ወረዳው በዛሬው ዕለት ያለው እንቅስቃሴ ካለፉት ቀናት የተሻለ መረጋጋት የሚታይበት መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል። “ከክልል የተላከ ግብረ ኃይል አለ። ከእኛ ጋር ተቀላቅለን፣ መከላከያም ጭምር ወደዚህ ከተሰማራው ጋር በየዕለቱ ውሎ እየተገመገመ ግብረ መልስ እየሰጠን እየሄድን ነው። ለዚህ ነው ጥሩ የሆነው” ሲሉ መረጋጋት የታየበትም ምክንያት ጠቅሰዋል። 

ፎቶ ፋይል፦ ኢታንግ ወረዳ

በኢታንግ ልዩ ወረዳ እንቅስቃሴዎች ወደ ነበሩበት እየተመለሱ ቢሆንም ከአራቱ ቀበሌዎች የተፈናቀሉት 650 እማ እና አባወራዎች ግን አሁንም በልዩ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል። “እዚያ ለመመለስ መልሶ መቋቋም ያስፈልጋል። ቤታቸው የለም ተቃጥሏል” ሲሉ ነዋሪዎቹ ለጊዜው በመጠለያው ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉን አቶ ኡቦንግ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)