የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ የሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪ፤ ዋነኛ ተግዳሮት እንደሆነ የተሃድሶ ኮሚሽን ገለጸ 

በአማኑኤል ይልቃል

የቀድሞ ተዋጊዎችን በትኖ ከህብረተሰቡ ለማዋሃድ የሚያስፈልገው “እጅግ ከፍተኛ ወጪ” ዋነኛ ተግዳሮት እንደሆነ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ። አጋር አካላት የገንዘብ እርዳታ ለመስጠት የገቡት ቃል፤ በተግባር መታየት እንዳለበትም ኮሚሽኑ አሳስቧል።

በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ የተቋቋመው ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ይህን ያስታወቀው፤ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሰኔ 5፤ 2015 በአዲስ አበባው ሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በተካሄደው የመልሶ ማቋቋም እና መገንባት ኮንፍረንስ ላይ ነው። በዚህ ኮንፍረንስ ላይ ጦርነት እና ግጭት ባስተናገዱ ስድስት ክልሎች ውስጥ የደረሰው የውድመት እና የኪሳራ መጠን እንዲሁም ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ይፋ ተደርጓል።

ለአምስት ዓመታት የሚቆየው የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ከሚከናወንባቸው ክልሎች ውስጥ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተካሄደባቸው ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ይገኙበታል። የኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ክልል የሚገኘው የኮንሶ ዞንም የዚህ እቅድ አካል እንደሆኑ በኮንፍረንሱ ላይ ተገልጿል።

ፎቶ፦ የገንዘብ ሚኒስቴር

በገንዘብ ሚኒስቴር በተዘጋጀው በትላንቱ ኮንፍረንስ ላይ የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታን በተመለከተ፤ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል ኃላፊዎች እንዲሁም የውጭ ሀገር ተቋማት ተወካዮች እና ባለሙያዎች የተሳተፉባቸው ውይይቶች ተካሄደዋል። በዚሁ የውይይት መድረክ፤ የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ ተቋማቸው ስለሚያከናውነው ስራ እና ስላሉበት ተግዳሮቶች ዝርዝር ገለጻ አቅርበዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ እንዲበተኑ ማድረግ እና እንደገና ወደ ህብረተሰቡ የማዋሃድ ሂደቶች፤ በኢትዮጵያም ሆነ “በሌሎች ቦታዎች” በሚካሄዱበት ወቅት “የተለያዩ ተግዳሮቶች” እንደሚያጋጥሟቸው ኮሚሽነሩ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል። በዚህ መሰል ሂደቶች ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች አቶ ተሾመ በቀዳሚነት የጠቀሱት፤ “ግጭት የማቆም ስምምነት ሙሉ ተግባራዊነትን” ነው።

በግጭት ማቆም ስምምነት “እያንዳንዱ ድንጋጌ” መፈጸም እንዳለበት የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የሚከናወነው ፕሮግራም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። የፌደራል መንግስት፣ የህወሓት አመራሮች ወይም የጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ ግጭት የማቆም ስምምነቱን “ሙሉ ለሙሉ ሲተገበር ለመመልከት የፖለቲካ ቁርጠኝነት” እንዳላቸው ለኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል።

ኮሚሽነር ተሾመ “እጅግ አሳሳቢው ተግዳሮት” ሲሉ በሁለተኛነት የጠቀሱት ጉዳይ፤ ሂደቱን ለመተግበር የሚያስፈልገው ገንዘብ “ከፍተኛነትን” ነው። እርሳቸው የሚመሩት ተቋም የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተን እና እንደገና ወደ ህብረተሰቡ የማዋሃድ ፕሮጀክትን ለመተግበር የሚያስፈልገው ወጪ መለየቱን ኮሚሽነሩ ቢናገሩም፤ የገንዘቡን መጠን ግን “ትልቅ” ከማለት ውጪ በአሃዝ ሳይገልጹ ቀርተዋል።

ከትላንት በስቲያ ይፋ በተደረገው የገንዘብ ሚኒስቴር የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ሰነድ ላይ፤ በተሃድሶ ኮሚሽኑ ፕሮግራም ውስጥ የሚካተቱት የቀድሞ ተዋጊዎች ብዛት 250 ሺህ የሚጠጋ እንደሆነ ሰፍሯል። የቀድሞ ተዋጊዎቹ ይገኙባቸዋል ከተባሉ ስምንት ክልሎች ዝርዝር ውስጥ፤ የሰሜኑን ጦርነት ያስተናገዱት የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ተካትተዋል። የኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎችም የቀድሞ ተዋጊዎች የሚገኙባቸው ክልሎች መሆናቸው በሰነዱ ላይ ተገልጿል። 

የተሃድሶ ኮሚሽን በስምንቱ ክልሎች ለሚያከናውነው ፕሮግራም የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 550 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ሁለት የኮሚሽኑ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ኮሚሽኑ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ከፍተኛ የሆነውን ገንዘብ የሚጠይቁት፤ የቀድሞ ተዋጊዎች እንደገና ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀል እና መልሶ ማቋቋም ስራዎች እንደሆነ ስማቸው እንዳይገልጽ የጠየቁ የኮሚሽኑ ምንጭ አስረድተዋል።

የቀድሞ ታዋጊዎችን የመበተን ስራ የሚጠይቀው የሎጂስቲክስ ወጪ መሆኑን የገለጹት እኚሁ ምንጭ፤ ቀሪዎቹ ሁለት ስራዎች ግን ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል። “በተለይ ስራ የሌላቸው ሰዎች ከሆኑ የሙያ ስልጠና ሰጥቶ በዚያ ስራ እንዲሰሩ [የሚደረግበት] ስለሆነ፤ እያንዳንዱ ስራ ለመነሻ ካፒታል የሚሰጣቸው ከፍ ስለሚል በአብዛኛው ወጪ የሚጠይቀው ይሄኛው ክፍል ነው” ሲሉም የመልሶ ማቋቋሙ ስራ ከፍ ያለ ገንዘብ የሚጠይቅበትን ምክንያት አብራርተዋል።

ኮሚሽነር ተሾመ፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተን ስራን ለማከናወነም “ትልቅ መጠን ያለው ገንዘብ” እንደሚያስፈልግ በትላንቱ ኮንፈረንስ ላይ ተናግረዋል። የተሃድሶ ኮሚሽን የመጀመሪያውን ዙር የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተን ስራ ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንዳለም ጨምረው ገልጸዋል። ይህ የመጀመሪያ ዙር ስራ መቼ እንደሚጀምር ከ“ኢትየጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ኮሚሽነር ተሾመ፤ “ያላለቀ ነገር” መኖሩን በመጥቀስ ለክንውኑ የጊዜ ሰሌዳ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንን ለማቋቋም ባለፈው ህዳር ወር ላይ የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን በጊዜያዊ እና ዘላቂ በሆነ መልኩ መልሶ ለመቀላቀል የሚውል ሀብት ከመንግስት እንደሚመደብ ደንግጎ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም “ከተለያዩ ህጋዊ የገቢ ምንጮች የሚሰበሰብ ሀብት” ስራውን ለማከናወን እንደሚውል በደንቡ ላይ ሰፍሯል።

የፌደራል መንግስት በ2016 በጀት ዓመት ለተሃድሶ ኮሚሽን ሊመደብለት ያቀደው የገንዘብ መጠን 30 ሚሊዮን ብር እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ከቀረበው የበጀት ረቂቅ ላይ ተመልክታለች። የኮሚሽኑን ፕሮግራም ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ ከአጋር አካላት ጋር “ገንቢ ግንኙነት” መኖሩን አቶ ተሾመ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከአጋር አካላት በኩል “ብዙ ቃል ኪዳኖች” መኖራቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ “የተቀናጀ ነገር እንፈልጋለን። ይህ ደግሞ ብዙ ስራ፤ ብዙ ትብብር ይጠይቃል” ሲሉ አክለዋል።

የተሃድሶ ኮሚሽን ለሚያከናውናቸው ተግባራት “አጋር አካላት” ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ኮሚሽነር ተሾመ በትላንቱ ኮንፍረንስ ላይም አንስተዋል። ሆኖም ይህ የአጋር አካላት ቃል በተግባር መገለጽ እንዳለበት ኮሚሽነሩ በኮንፍረንሱ ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ “ቅድሚያ የሚሹ ተወዳዳሪ ጉዳዮች” (competing priorities) መኖራቸውን የገለጹት አቶ ተሾመ፤ ይህም ለኮሚሽኑ የሚደረገው  የገንዘብ ድጋፍ ላይ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ እንዲበተኑ የማድረግ እና እንደገና ወደ ህብረተሰቡ የማዋሃድ ፕሮግራም ላይ በጊዜው የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ ከሌለ እና ድጋፉ በቂ ካልሆነ፤ ሂደቱ “ከጅምሩ የከሸፈ ይሆናል” ሲሉም ኮሚሽነር ተሾመ አስረግጠው ተናግረዋል። ኮሚሽኑ አሁን ከአጋሮች ጋር ባለው ግንኙነት ግን ሂደቱ ይህ ይገጥመዋል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።፡

ፎቶ፦ ኪራ ስሚዝ ሲንድበርግ ፤ በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር

ኮሚሽነር ተሾመ በተግዳሮትነት ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ ፕሮግራሙ በሚከናወንበት ጊዜ በቀድሞ ተዋጊዎች፣ ቤተሰቦቻቸው እና የሚኖሩበት ማህበረሰብ ላይ የሚፈጠርን “ከፍተኛ ግምት” ነው። እነዚህ አካላት “ከፍተኛ ድጋፍ” እንደሚጠብቁ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ይህ አይነቱ ግምት “መገራት” እንዳለበት ገልጸዋል። “ይህ ካልሆነ የከባድ ውዝግብ ምንጭ ይሆናል። በፕሮግራሙ ትግበራ ላይም ጉልህ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል” ሲሉም ተደምጠዋል።

በተሃድሶ ኮሚሽን ፕሮግራም ውስጥ የሚካተቱ የቀድሞ ተዋጊዎች፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ የሚፈጠር “የአቅርቦት እና ሎጂስቲክስ” ችግርም በኮሚሽነር ተሾመ በተግዳሮትነት የተጠቀሰ ሌላኛው ጉዳይ ነው። የተሃድሶ ኮሚሽን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በትብብር እንደሚሰራ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ይህን በተመለከተ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ሰራዊቱ ያሉትን “የአቅርቦት እና ሎጂስቲክስ” መዋቅሮች በመጠቀም የሚቀረፉ ይሆናሉ ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)