ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ግብይት ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቋ ተገለጸ 

በአማኑኤል ይልቃል

ኢትዮጵያ በቀጣዩ የ2016 በጀት ዓመት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና፤ በአህጉሪቱ ካሉ ሀገራት ጋር ግብይት እንድትጀምር እቅድ መያዙን እና ዝግጅቶችም እየተጠናቀቁ መሆኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ኢትዮጵያ በአህጉራዊው ነጻ የንግድ ቀጣና የምትገበያያቸውን የምርቶች እና አገልግሎቶች አይነት፤ በቀጣዩ ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በሚካሄድ የአፍሪካ የንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ እንደምታቀርብም ገልጸዋል። 

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት፤ በአህጉሩ ስር ባሉ ሀገራት መካከል የሚደረጉ የንግድ ግንኙነቶች ያሉባቸውን ተግዳሮች በመቅረፍ የሀገራቱን የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ ያለመ የአፍሪካ ህብረት ፕሮጀክት ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ 54 የአፍሪካ ሀገራት የፈረሙት ይህ ስምምነት፤ ሀገራቱ እርስ በእርስ በሚገበያዩት ወቅት የሚጣለውን ቀረጥ የማስወገድ እቅድ አለው።

በነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ መሰረት፤ የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ የሚገበያዩዋቸውን 90 በመቶ ምርቶች እና አገልግሎቶች በአስር ዓመት ውስጥ ከቀረጥ ነጻ ያደርጋሉ። በ13 ዓመት ውስጥ ደግሞ ተጨማሪ ሰባት በመቶ ምርቶች እንዲሁ ከቀረጥ ነጻ አድርገው ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንዲያስገቡ ይጠበቃል። ሀገራቱ ቀረጥ መጣል የሚችሉት በመረጧቸው ሶስት በመቶ የሚሆኑ ምርቶች ላይ ብቻ ነው።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ

በሂደት ቀረጥ ነጻ የሚያደርጓቸውን እና የማያደርጓቸው ምርቶች አቅርበው ድርድር ያደረጉ የአፍሪካ ሀገራት፤ ከታህሳስ 2013 ዓ.ም ጀምሮ እርስ በእርስ መገበያየት ጀምረዋል። በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ ከታሪፍ ነጻ የምታደርጋቸውን ምርቶች እስካሁን በይፋ ያላሳወቀችው ኢትዮጵያ፤ ወደ ግብይት ስርዓቱ መግባት አልቻለችም። 

የኢትዮጵያ መንግስት ሳያቀርብ የዘገየውን የምርቶች ዝርዝር ከ10 ቀናት በኋላ ላይ በኬንያ በሚደረግ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ለማቅረብ መዘጋጀቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሳሁን አስታውቀዋል። አቶ ካሳሁን ይህንን ያስታወቁ፤ ትላንት አርብ ሰኔ 23፤ 2015 በፓርላማ በተካሄደ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው። በተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ የትላንቱን ስብሰባ የጠራው፤ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የ11 ወራት የስራ አፈጻጸም ለመገምገም ነበር።  

በዚሁ ስብሰባ ላይ፤ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የምታደርጋቸውን የንግድ ግንኙነቶች የተመለከቱ ጉዳዮች ተነስተዋል። ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ካሳሁን፤ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ላይ ለግብይት የሚቀርቡ ከስድስት ሺህ በላይ የእቃዎች “የስሪት ሀገር ልየታ” (country of origin) መደረጉን ለፓርላማ አባላት ገልጸዋል። “የትኛው ምርት ነጻ ይሁን፣ የትኛው ምርት ለሚቀጥሉት ጊዜያት ይያዝ፣ የትኛው ምርት እስከ ዝንተ ዓለም አንከፍተውም የሚለው ጉዳይ ሰፊ ክርክር” እንደተደረገበትም አስረድተዋል።

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

በመጪው ሐምሌ 3 እና 4፤ 2015 በኬንያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ የንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና “ስራ ለመጀመር የሚያስችላትን ዝግጅት ማጠናቀቋን እንደምታበስርም” አቶ ካሳሁን ለንግድ እና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የትኛዎቹን ምርት እና አገልግሎቶች፤ በቅድሚያ ከቀረጥ ነጻ ለማድረግ እንደወሰነች ግን ሚኒስትር ዴኤታው በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል። 

በአህጉራዊው የንግድ ስምምነት አማካኝነት ለግብይት የሚቀርቡ ምርቶች እና አገልግሎቶች ዝርዝር በብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ መጽደቁን አቶ ካሳሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በኬንያው ጉባኤ፤ ኢትዮጵያ በነጻ የንግድ ቀጣና አማካኝነት የምትገበያይባቸውን ምርቶች እና አገልግሎቶች የያዘ ሰነድ እንደምታቀርብ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ይህንን ዝርዝር ካቀረበች በኋላ “exclusive negotiation” ለማድረግ የሚፈልጉ ሀገራት ካሉ “እድል” ተሰጥቶ ድርድር እንደሚካሄድ አብራርተዋል። 

በዚህ አይነቱ ድርድር፤ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ዝርዝር ላይ ሀገራት እንዲሻሻልላቸው የሚፈልጓቸውን ሀሳቦች ሊነሱ እንደሚችሉ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። ይህ ድርድር ከተጠናቀቀ በኋላ፤ በ2016 በጀት ዓመት ወደ ግብይት ማዕቀፉ ለመግባት እቅድ መያዙን አቶ ካሳሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በእርሳቸው የሚመራ እና ይህንኑ የሚከታተል “ብሔራዊ የትግበራ ኮሚቴ” (national implementation committee) መቋቋሙን እና ቅድመ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁንም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)