የጉራጌ ዞን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካይ፤ ለሁለተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

በሃሚድ አወል

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ትላንት ቅዳሜ ሰኔ 24፤ 2015 ምሽት በፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠበቃቸው እና ባለቤታቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። አቶ ታረቀኝ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ እና በ“ፒክ አፕ” መኪና የተጫኑ የጸጥታ አባላት በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ አካባቢ ወደሚገኘው የአቶ ታረቀኝ መኖሪያ ቤት የደረሱት፤ ትላንት ከምሽቱ 2፡30 ገደማ እንደነበር ባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ መርሻ ተናግረዋል። የጸጥታ አባላቱ “ከፌደራል ፖሊስ ነው የመጣነው” ሲሉ መስማታቸውን የጠቀሱት አዜብ፤ “ለጥያቄ እንፈልግሃለን” ብለው አቶ ታረቀኝን አብረዋቸው እንዲሄዱ ጥያቄ ማቅረባቸውን አክለዋል። 

ባለቤታቸው “እኔ ያለመከሰስ መብት አለኝ፤ የህዝብ ተወካይ ነኝ” ቢሉም፤ ፖሊሶቹ “እሱን እዚያ ታወራለህ፤ ተነስ ዝም ብለህ” የሚል ትዕዝዝ መስጠታቸውን አዜብ ገልጸዋል። የተሻሻለው የደቡብ ክልል ህገ መንግስት፤ የክልሉ ምክር ቤት አባል “ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀል አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል። 

አቶ ታረቀኝ የደቡብ ክልልን ምክር ቤት የተቀላቀሉት፤ በ2013 ዓ.ም በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ተቃዋሚውን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲን (ኢዜማ) ወክለው በመወዳደር ነው። የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባሉ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ፤ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መወሰዳቸውን ባለቤታቸው ተናግረዋል። 

ዛሬ እሁድ ረፋድ ላይ ምግብ እንዳደረሱላቸው እና በወንጀል ምርመራ ቢሮው በአካል እንዳገኟቸውም ጨምረው ገልጸዋል። የአቶ ታረቀኝን እስር በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ፤ ስለ ጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው እና በነገው ዕለት አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል። 

የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባሉ በዚህ ዓመት ለእስር ሲዳረጉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። አቶ ታረቀኝ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ህዳር ወር አጋማሽ ላይ በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ፤ ወደ ሀዋሳ ከተማ ተወስደው ለአንድ ወር ገደማ ያህል በእስር ላይ ቆይተዋል። አቶ ታረቀኝ በወቅቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት በጉራጌ ዞን “ወልቂጤ ከተማ የተቀሰቀሰን ሁከት መርተዋል” በሚል ተጠርጥረው መሆኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስታውቆ ነበር። 

የጉራጌ ዞን በክልልነት ከመደራጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፤ ካለፈው 2014 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በወልቂጤ ከተማ ተደጋጋሚ የስራ ማቆም እና ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማዎች ሲደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል። አቶ ታረቀኝ የጉራጌ ዞንን በክልልነት መደራጀት ምላሽ እንዲያገኝ፤ በደቡብ ክልል ምክር ቤት በተደረጉ ስብሰባዎች እና በሌሎችም መድረኮች ተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብ የሚታወቁ ናቸው። የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባሉ፤ ከዚህ ቀደም በሀዋሳ ታስረው ከቆዩበት የተለቀቁት የ100 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)