የጉራጌ ዞን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካይ፤ “በመታወቂያ ዋስ” ከእስር ተለቀቁ 

በሃሚድ አወል

ለሁለት ቀናት በእስር የቆዩት የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ታረቀኝ ደግፌ፤ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 27፤ 2015 አመሻሽ ላይ “በመታወቂያ ዋስ” ከእስር መፈታታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። አቶ ታረቀኝ ዛሬ ረፋድ ላይ፤ የደቡብ ክልል ፖሊስ አባላት ወዴት እንደሆነ ወደ አላወቁት  ቦታ “ሊወስዷቸው” ሞክረው እንደነበርም ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞንን በመወከል የደቡብ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፌደራል ፖሊስ የተያዙት ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 24 ምሽት 2፡30 ገደማ ነበር። አቶ ታረቀኝ ከመኖሪያ ቤታቸው “ትፈለጋለህ” ተብለው ከተያዙ በኋላ፤ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

አቶ ታረቀኝ በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው የመጡትን የፌደራል ፖሊስ አባላት የፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ይዘው እንደሆነ መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።  ለዚህ ጥያቄያቸው ምላሽ አለማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ታረቀኝ፤ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባልነት መታወቂያቸውን በማሳየት “ያለመከሰስ መብት ያላቸው” መሆኑን ማስረዳታቸውን ጠቅሰዋል። ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳበት “ወረቀት” እንዳለ ቢጠይቁም፤ በተመሳሳይ መልኩ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አብራርተዋል። 

የደቡብ ምክር ቤት አባሉ ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እሁድ ምሽት ከገቡ በኋላ፤ የጣት አሻራ እና የግል መረጃዎችን ከማስሞላታቸው ውጪ ቃላቸውን ለመርማሪ አለመስጠታቸውን አክለዋል። አቶ ታረቀኝ በወንጀል ምርመራ ቢሮ ስለነበራቸው ቆይታ ሲያስረዱ፤ “ቃልም አልተቀበሉኝም። በምን ምክንያት እንደታሰርኩም አልነገሩኝም። በተደጋጋሚ ‘በምን ምክንያት ነው [የታሰርኩት]’ ብዬ [ጠይቄ] ነበር። ‘እኛ አናውቅም’ ነው ያሉኝ” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ  ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

አቶ ታረቀኝ በዛሬው ዕለት “በመታወቂያ ዋስ” ከእስር እንዲወጡ ከመደረጋቸው ከአራት ሰዓት ገደማ በፊት፤ የደቡብ ክልል ፖሊስ አባላት እርሳቸው ወዳላወቁት ቦታ “ሊወስዷቸው” ሞክረው እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም “የትም መሄድ አልፈልግም” በሚል እምቢታቸውን በመግለጻቸው፤ ሙከራው አለመሳካቱን አስረድተዋል። ይህንን የአቶ ታረቀኝ ገለጻ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከሌላ ወገን ማረጋገጥ አልቻለችም። 

በ2013 ዓ.ም በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ፤ ከጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲን (ኢዜማ) ወክለው የደቡብ ክልል ምክር ቤትን የተቀላቀሉት አቶ ታረቀኝ፤ ከዚህ ቀደም ለአንድ ወር ገደማ ታስረው በ100 ሺህ ብር ዋስትና መፈታታቸው ይታወሳል። አቶ ታረቀኝ ከአዲስ አበባ ተወስደው በእስር በቆዩበት በሀዋሳ ከተማ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፤ ፖሊስ በጉራጌ ዞን “ወልቂጤ ከተማ የተቀሰቀሰን ሁከት መርተዋል” በሚል መጠርጠራቸውን ገልጾ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)