የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ 17 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት አጸደቀ  

በአማኑኤል ይልቃል

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ለ2016 በጀት ዓመት የሚሆን 17 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካጸደቀው በጀት ውስጥ 74 በመቶው የሚሸፈነው የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል ከሚያስተላልፈው የድጋፍ በጀት ነው። 

የትግራይ ክልል የሰሜኑ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በመደበኛ ሁኔታ በጀት ያጸደቀው፤ ባለፈው ሳምንት አርብ ሐምሌ 14፤ 2015 እንደሆነ የክልሉ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ሀንሳ ተክላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለክልሉ መንግስት የሚመደበው በጀት ከዚህ ቀደም ይጸድቅ የነበረው በትግራይ ክልል ምክር ቤት ነበር። 

የ2016 በጀት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ የጸደቀው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ህግ የማውጣት ስልጣኑን ለክልሉ ስራ አስፈጻሚ አካል በመስጠቱ መሆኑን ኮሚሽነሯ አስረድተዋል። የክልሉ ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ  ከመዋቀሩ ከሁለት ወር ገደማ በፊት ነው። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላት ማንነት ይፋ የተደረገው በመጋቢት ወር መጨረሻ በመቐለ ከተማ በተካሄደ ስነ ስርዓት እንደነበር ይታወሳል። 

በዚህ መልኩ ስራ የጀመረው የክልሉ ካቢኔ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባደረገው ስብሰባ፤ ለ2016 በጀት ዓመት 17 ቢሊዮን ብር በጀት ማጽደቁን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባል የሆኑት ወ/ሮ ሀንሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ በጀት የሰሜኑ ጦርነት ከመቀስቀሱ አስቀድሞ ለ2013 በጀት ዓመት ጸድቆ ከነበረው “ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ” ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁመዋል። የአሁኑ በጀት በ2012 በክልሉ ምክር ቤት ከጸደቀው በጀት ጋር ሲነጻጸር ያለው ልዩነት የ300 ሚሊዮን ብር ገደማ ብቻ ነው።

ከተያዘው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ተግባራዊ በሚደረገው የትግራይ ክልል የ2016 በጀት፤ ከፍተኛው መጠን የተመደበው ለሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ ነው። በበጀት ዝርዝሩ ላይ ለክልሉ ሰራተኞች ደመወዝ፣ ለመጠባበቂያ የሚያዝ ገንዘብ እና “ለተለያዩ ወጪዎች” የተያዘው አጠቃላይ ገንዘብ 14.4 ቢሊዮን ብር ነው። የትግራይ ክልል ለ2016 የካፒታል በጀት የመደበው 1.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን “ለስራ ማስኪያጃ” የያዘው የገንዘብ መጠን ደግሞ አንድ ቢሊዮን ብር መሆኑን ከክልሉ ፕላን ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ለ2016 ካጸደቀው በጀት ውስጥ አብዛኛውን መጠን ለመሸፈን ያቀደው፤ ከፌደራል መንግስት ከሚያገኘው የድጋፍ በጀት ነው። የፌደራል መንግስት ለ2016 በጀት ዓመት ለትግራይ ክልል የመደበው የበጀት ድጎማ 12.59 ቢሊዮን ብር ነው። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ አራት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በራሱ ለመሰብሰብ አቅዷል።   

ወ/ሮ ሀንሳ “3.7 ቢሊዮን ብር ግብር እንሰበስባለን ተብሎ ነው የታሰበው። በክልሉ የደቀቀ ኢኮኖሚ እንዳለ ይታወቃል። ይሄንን ራሱ መሰብሰብ ይቻላል ወይ? [የሚለው] ሌላ ፈተና ነው። እንደዚያም ሆኖ ‘የተቻለው ይደረጋል’ ተብሎ ነው የጸደቀው” ሲሉ በእቅድ ደረጃ የተቀመጠው ገቢ ስለመገኘቱ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት የክልሉ መንግስት ከግብር “ቢያንስ ስድስት ቢሊዮን ብር” ይሰበስብ እንደነበር የጠቀሱት ኮሚሽነሯ፤ በአሁኑ ሰዓት ያለው የክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይህንን ያህል ገንዘብ ማመንጨት እንደማይችልም ጠቁመዋል።

“በጀት ሲጸድቅ ብዙ ምንጮች ይኖሩ ነበር። ከህዝብ መዋጮ ራሱ የሚጠበቅ ነገር ይኖራል። በኖርማል ጊዜ፤ ከግሉ ሴክተር ራሱ ልትበደር የምትችልበት ሁኔታ አለ። አሁን ሁሉም እርዳታ የሚፈልግ ነው” ሲሉም ክልሉ የበጀት ምንጩን ከማስፋት አንጻር የገጠመውን ችግር አብራርተዋል። በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ከቀያቸው ተፈናቅለው እርዳታ የሚሹ የክልሉ ነዋሪዎች ብዛት 950 ሺህ እንደሆነ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል። ከዚህ ቀደም ተፈናቅለው ከነበሩ የክልሉ ነዋሪዎች ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ያህሉ ወደ ቀያቸው ቢመለሱም እነርሱም ጭምር እርዳታ እንደሚሹ ኮሚሽኑ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)