ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ በመጪው ዓመት ጥር ወር ዋናውን ኮንፍረንስ ለማካሄድ “የሚቻለውን ጥረት እያደረግኩ ነው” አለ 

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመጪው ዓመት ጥር ወር ላይ ዋናውን የምክክር ጉባኤ ለመጥራት “የሚቻለውን ጥረት” እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ከነገ ነሐሴ 18፤ 2015 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የጉባኤውን ተሳታፊዎች መለየት እንደሚጀምርም ይፋ አድርጓል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህን ይፋ ያደረገው፤ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 17 በዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ በአዋጅ የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ እስካሁን ድረስ በአምስት ክልሎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር የጉባኤ ተሳታፊዎች ልየታን አከናውኗል።

ኮሚሽኑ የጉባኤ ተሳታፊዎችን የለየባቸው አካባቢዎች፤ በሐረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ናቸው። በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ፤ “እስከ ጥር ድረስ ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ኮንፍረንስ ለመጥራት የሚቻለንን ጥረት እያደረግን ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋነኛውን ሀገራዊ ምክክር ኮንፍረንስ ለማካሄድ አቅዶ የነበረው ባለፈው ህዳር ወር ነበር። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባሉ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት በእቅዱ መሰረት መጓዝ አለመቻሉን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ሀገራዊ ምክክሩን የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በአምስት ወራት በማራዘም ኮንፍረሱን በግንቦት ወር እንደሚያካሄድ አስታውቆ ነበር። 

ይህ የኮሚሽኑ እቅድም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አልቻለም። የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ከተያዘለት ጊዜ በላይ መዘግየቱ፤ ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ በተካሄደ በፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ጥያቄ አስነስቶ ነበር። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በዚህ ስብሰባ ላይ ለተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ካሉት “ተጨባጭ ሁኔታዎች አንጻር” በዕቅድ የተቀመጡ ተግባራት “ለትግበራ ረዘም ያለ ጊዜያትን ወስደዋል” ሲል ሂደቱ የዘገየበትን ምክንያት አስረድቶ ነበር።  

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር በዛሬው መግለጫቸው ሀገራዊ የምክክር ኮንፈረንሱን ከስድስት ወራት በኋላ ለመጥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ቢጠቁሙም፤ “ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ ኮሚሽኑን ተገማች ያልሆኑ ክሰተቶች ሊፈትኑት እንደሚችሉ አመላክተዋል። “በእኛ ግምት እና በእኛ ዕቅድ መሰረት ያንን ለማድረግ ነው የምናስበው” ሲሉ ኮሚሽነሯ አክለዋል። 

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ችግሮች ስራውን “አዳጋች እያደረጉበት” አስታውቆ ነበር። ኮሚሽኑ በመላው ሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች “ያላንዳች ቅደመ ሁኔታ ቆመው” “በአስቸኳይ” በምክክር እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል።

የምክክር ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው ባለድርሻ አካላትን “በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየት እና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን” መግለጹ አይዘነጋም። በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች፤ ከነሐሴ ሁለቱ የኮሚሽኑ ጥሪ በኋላ በተቋሙ በኩል የተሰሩ ስራዎችን ስለመኖራቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “እኛ ቀጥታ አስታራቂዎች አይደለንም። [ነገር] ግን የተለያዩ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ መገኘት እንዲችሉ የሚደረገውን ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “ከእኛ ጋር በቀጥታ አብሮ ለመስራት ዳተኛ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚሁም ደግሞ ችግራችንን በትጥቅ ትግል ነው የምንፈታው ብለው የተሰማሩ ኃይሎችንም ጭምር ለማነጋገር ወስነናል” ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሯ አክለዋል። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህን ውሳኔ የወሰነው “አካታች መሆን ስላለበት” እንደሆነ ሂሩት ጠቁመዋል። አሁን ያለው ሁኔታ በዚሁ መልክ ከቀጠለ ተቋሙ “ስራውን መስራት የማይችልበት ደረጃ ላይ የሚደርስ” መሆኑም ለውሳኔው መወሰን ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል። በታህሳስ 2014 በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ስራዎቹን ሲያከናውን የቆየው በሶስት ምዕራፎች ከፋፍሎ ነበር።

በመጀመሪያው የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል  የኮሚሽኑን ጽህፈት ቤት ማደራጀት እና ተሞክሮዎችን መሰብሰብ ተጠቃሽ ናቸው። ኮሚሽኑ “የዝግጅት ምዕራፍ” ብሎ በሚጠራው በሁለተኛው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ ማሰባሰብን ያከናውናል። በአምስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የሀገራዊ ምክክር ኮንፍረንስ ተሳታፊዎችን የመለየት ስራን ያጠናቀቀው ኮሚሽኑ፤ ከነገ ሐሙስ ነሐሴ 18 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተመሳሳዩን ሂደት እንደሚጀምር በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ለሚያካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ “እገዛ የሚያደርጉ” ያላቸውን ተባባሪ አካላት መለየቱንም ገልጿል። ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት የተሳታፊዎች ልየታን ባካሄደባቸው ሶስት ክልሎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር በተመሳሳይ “ተባባሪ አካላትን” አሳትፎ ነበር። “ተባባሪ አካላት” በሚል በወቅቱ ኮሚሽኑ ካሰተፋቸው ተቋማት መካከል፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲሁም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ይገኙበታል፡፡

በመዲናዋ የሚካሄደው የታሳታፊዎች ልየታ በሁለት ምዕራፍ እንደሚከናወን በዛሬው መግለጫ ላይ ተነግሯል። በመጀመሪያው ምዕራፍ የተካተተው ለ“ተባባሪ አካላት” የሚሰጠው ስልጠና፤ በአዲስ አበባው ጊዮን ሆቴል ከሐሙስ ጀምሮ  ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥም ተገልጿል። 

በሁለተኛው የተሳታፊዎች ልየታ ምዕራፍ ከተካተቱ ተግባራት መካከል “የህብረተሰብ ተወካዮችን ማስመረጥ” የሚለው ይገኝበታል። እነዚህ ተወካዮች የሚመረጡት በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 119 ወረዳዎች ነው። ከእነዚህ ወረዳዎች የተመረጡት ተወካዮች፤ በአጀንዳ ማሰባሰብ እና በዋና የምክከሩ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን የሚመርጡ ይሆናል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክለውበታል]