በሀዋሳ ከተማ ያሉ የንግድ ተቋማት በአንድ ወር ውስጥ የደህንነት ካሜራ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ መመሪያ ወጣ  

በሃሚድ አወል

የሲዳማ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የንግድ ተቋማት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የደህንነት ካሜራ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ መመሪያ አወጣ። መመሪያውን ተግባራዊ የማያደርጉ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ላይ የእስር አሊያም የገንዘብ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ቢሮው መመሪያውን ይፋ ያደረገው፤ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 17፤ 2015 በሀዋሳ ከተማ ከሚገኙ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ነው። የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሀዋሳ የሚገኙ የንግድ ተቋማት፤ የደህንነት ካሜራ እንዲገጥሙ የሚስገድደው መመሪያ የወጣው በሁለት ምክንያቶች ነው ተብሏል።

በሀዋሳ ከተማ በሚገኙ አንዳንድ ድርጅቶች ፊት ለፊት “የሞተር ሳይክል ስርቆቶች” በተደጋጋሚ እንደሚፈጸሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፤ ይህንን ድርጊት እና በድርጅቶቹ ውስጥ በሀሰተኛ የገንዘብ ኖት የሚደረጉ ግብይቶችን “ለመቆጣጠር” መመሪያው መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በአዲሱ መመሪያ መሰረት በከተማይቱ የሚገኙ የንግድ ተቋማት በድርጅታቸው ውስጥ እና ወደ ውጭ የሚመለከቱ የደህንነት ካሜራዎችን መግጠም ይኖርባቸዋል። 

የንግድ ተቋማቱ ውጭ የሚገጥሟቸው የደህንነት ካሜራዎች፤ “በአራቱም አቅጣጫ ቢያንስ 500 ሜትር ርቀት ላይ ያሉ ጉዳዮችን ጭምር የሚቆጣጠር” መሆን እንዳለበት አቶ አለማየሁ አስረድተዋል። የደህንነት ካሜራዎቹ መገጠም “የጸጥታ ኃይሉ በሌለበት ጊዜ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን [እና] ስውር ወንጀሎችን ‘ሲስተማቲካል’ በሆነ መንገድ ለመቀነስ ይረዳል” ሲሉም የቢሮ ኃላፊው መመሪያው ያስፈለገበትን ምክንያት አብራርተዋል።

በሀዋሳ ከተማ ያሉ የንግድ ተቋማት አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ አንድ ወር የጊዜ ገደብ እንደተሰጣቸው በዛሬው ስብሰባ ላይ ተነግሯቸዋል። ይህንን መመሪያ ተግባራዊ የማያደርጉ ተቋማትን በተመለከተ “ዝርዝር የቅጣት ደረጃ” በቀጣይ ቀናት እንደሚወጣ የሲዳማ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“እስራት እና የገንዘብ መቀጮን ሊያካትት ይችላል” የተባለውን የቅጣት ደረጃ እና አፈጻጸሙን የማውጣት ስልጣን የተሰጠው፤  መመሪያውን ለማስፈጸም ለተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ነው። “ከዚህ መመሪያ የሚያፈነግጥ ይኖራል የሚል ግምት የለንም” የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ “የመመሪያውን ውሳኔዎች ተላልፈው በሚገኙ ላይ በየደረጃው የተቀመጠውን የቅጣት ስርዓት ተከትለን ተግባራዊ እናደርጋለን” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ፎቶ፦ የሲዳማ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ

በዛሬው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙ ሁለት የንግድ ድርጅት ባለቤቶች፤ የቢሮውን መመሪያ በበጎ እንደሚመለከቱት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ዘካርያስ ካሳ የተባሉ የሬስቶራንት እና ላውንጅ ባለቤት፤ ከመመሪያው መውጣት በኋላ የደህንነት ካሜራ ለመግጠም ማቀዳቸውን አስረድተዋል። የመመሪያውን “አስፈላጊነት እናውቃለን” የሚሉት አቶ ዘካርያስ፤ “ጊዜ ገደብ ባያስቀምጡ ግን ጥሩ ነበር” ሲሉ በአንድ ወር ተፈጻሚ ይሆናል መባሉ የፈጠረባቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። 

የሬስቶራንት እና ላውንጅ ባለቤቱ “ወቅቱ ግብር የሚከፈልበት መሆኑ”፤ “ሁሉም ሰው አንድ ላይ ሊገዛ ሲወጣ ገበያ ላይ ሊወደድ ይችላል” የሚሉት የቅሬታቸው ምንጮች ናቸው። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የጠቅላላ ንግድ ድርጅት ባለቤትም የአቶ ዘካርያስን ስጋት ይጋራሉ። የካፍቴሪያ ዕቃዎች እና የፈሳሽ ሳሙና ሽያጭ ላይ የተሰማራን ድርጅት የሚመሩት እኚሁ ግለሰብ፤ መጪው አንድ ወር ግብር የሚከፈልበት ወቅት በመሆኑ “ነጋዴዎችን ላላሰቡት ወጪ ያጋልጣቸዋል” ባይ ናቸው።

የንግድ ድርጅቱ ባለቤት የመመሪያው አስገዳጅነትም ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል። ሀዋሳ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው የንግድ ተቋማቸው የደህንነት ካሜራ የገጠሙት ከአምስት ዓመታት በፊት እንደሆነ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው፤ የጊዜው መቆየት በመመሪያው ላይ የተቀመጠውን መስፈርት ላያሟላ ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። ግለሰቡ ከመጋዘናቸው በተጨማሪ በሱቃቸው ውስጠኛው ክፍል የገጠሙት የደህንነት ካሜራ መቃኘት የሚችለው በመቶ ሜትር ርቀት ያለውን አካባቢ ብቻ መሆኑ፤ በእርግጥም በመመሪያው ከተቀመጠው መስፈርት የማያሟላ ያደርገዋል። 

የንግድ ተቋማት ባለቤቶች ቅሬታዎች ያቀረቡበትን ይህን መመሪያ በተመለከተ ከ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የሲዳማ ክልል ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ደመቀ ደፋሮ፤ “እኛ ጋር የደረሰን ምንም ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ደመቀ “እኛ ጋር ምንም ነገር ባልመጣበት ሁኔታ መግለጫ መስጠት አንችልም” በማለትም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)