በአማኑኤል ይልቃል
የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ “የዶክትሬት ዲግሪ አቻ በሆነ ደረጃ” ተማሪዎችን ማሰልጠን እንደሚጀምሩ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ። የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የ“ወጪ መጋራት ስርዓት” ውስጥ እንደሚገቡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
“ከከፍተኛ ትምህርት በታች” በሆነ ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች ተማሪዎችን የሚያሰለጥኑት የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት፤ “በገበያ ፍላጎት የሚመራ አስፈላጊ የሰው ኃይል የማፍራት” ኃላፊነት በአዋጅ የተጣለባቸው ናቸው። ተቋማቱ እና የሚሰጡት ስልጠና ባለፉት ለሶስት አስርት ዓመታት ገደማ ሲመራ የቆየው፤ በ1986 ዓ.ም. የወጣውን የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲን መሰረት በማድረግ ነበር።
እስካሁን ባለው አሰራር፤ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት ስልጠና ሲሰጡ የቆዩት “ከአንድ እስከ አምስት” ባሉ ደረጃዎች ነው። የተቋማቱ የመጨረሻ የስልጠና እርከን የሆነው “ደረጃ አምስት”፤ በመደበኛው የትምህርት ስርዓት “አድቫንስድ ዲፕሎማ” የተባለው የትምህርት ደረጃ አቻ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሰኞ የካቲት 20፤ 2015 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ያጸደቀው አዲሱ “የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ” ግን ተቋማቱ የሚሰጡትን የስልጠና ደረጃ በሶስት አሳድጎታል። አዲስ የተጨመሩት ሶስት ደረጃዎች፤ በመደበኛው የትምህርት ስርዓት ውስጥ “የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ” የሚል ስያሜ ያላቸው ደረጃዎች አቻ እንደሆኑ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ይህንን የገለጸው፤ አዲሱን ፖሊሲ እና የዘንድሮ የተቋማቱን መቁረጫ ነጥብ አስመልክቶ ትላንት ረቡዕ የካቲት 22፤ 2015 በዋና መስሪያ ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና የሚወስዱ ተማሪዎች በእነዚህ ደረጃዎች እንዲሰለጥኑ መደረጉ፤ ተቋማቱ “ያልተሳካላቸው ሰዎች ማረፊያ ናቸው” የሚለውን አስተሳሰብ የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል። የአዲሶቹ ደረጃዎች መጨመር “ዘርፉን ተወዳዳሪ፣ ተፈላጊ በማድረግ ረገድ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል” ሲሉም አስረድተዋል።
በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት የትምህርት እና ስልጠና ማዕከላት ስርዓት “flexible” እንደሚሆን የገለጹት የሚኒስቴሩ የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ተሻለ በሬቻ፤ ሁሉንም ደረጃዎች ለማጠናቀቅ የሚወስደው ጊዜ “እንደሰልጣኙ” የሚወሰን መሆኑን አስረድተዋል። ይሁንና ሰልጣኞች በሁሉም ደረጃዎች ምዘናዎችን ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል።

በቅርቡ የሚጸድቀው “የትምህርት እና ስልጠና የብቃት ማዕቀፍ”፤ በአዲሱ ፖሊሲ ላይ የተካተቱትን ሶስት አዲስ ደረጃዎችን የተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮችን እንደሚይዝ ሚኒስትር ዲኤታው አክለዋል። በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት ሰልጣኞች የዶክትሬት ዲግሪ አቻ የሆነ ትምህርት እንደሚያገኙ የጠቀሱት የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴሯ፤ ሆኖም የእውቀቱ ስያሜ አሁን በስራ ላይ ባሉት የዲግሪ አይነቶች እንደማይጠራ አስታውቀዋል።
“ስያሜውን ዲግሪ፣ ማስተርስ፣ ዲፕሎማ አንለውም። ምክንያቱም እርሱን የሚል ሌላ ዘርፍ አለ። የትምህርት፣ የመረጃ፣ የዕውቀት ዘርፉ እርሱን ይላል። የእኛ ዕውቀት ሲደመር ክህሎት ስለሆነ ክህሎትን የመሰለ ስያሜ ያስፈልገናል። ደረጃ፣ level፣ እርከን የሚለው ምሉዕ ነው ማለት ነው” ሲሉ ሙፈሪያት አብራርተዋል።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በአዲሱ ፖሊሲ ላይ የተቀመጡ ለውጦችን ለመተግበር፤ የስልጠና ተቋማቱን መልሶ የማደራጀት ስራ ሲያከናውን እንደቆየ በትላንትናው መግለጫ ተገልጿል። ለዚሁ ተብለው የሚከናወኑ ዝግጅቶች በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቁ የጠቆሙት ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር ተሻለ፤ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት በአዲሶቹ ደረጃዎች ሰልጣኞችን መቀበል እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማትን አስመልክቶ አዲሱ ፖሊሲ ካመጣቸው ለውጦች ውስጥ ሌላኛው፤ የተቋማቱ ስልጠና 70 በመቶ “ተግባር ተኮር” እንዲሆን መደረጉ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተነስቷል። ይህ አካሄድ ተጨማሪ ወጪዎችን የሚጠይቅ መሆኑ በሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ተገልጿል። የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት “ከፍተኛ የሆነ” ቴክኖሎጂ እና ማሽነሪ የሚጠቀሙ ከመሆኑ አንጻር፤ ስልጠናው “በባህሪው በጣም ውድ” እንደሆነ ዶ/ር ተሻለ አስረድተዋል።
“ይህን ትልቅ ሀብት በመንግስት ብቻ መሸፈን አይቻልም። ዜጎችም በተወሰነ ደረጃ cost share እያደረጉ መሄድ ይኖርባቸዋል” ሲሉ የ“ወጪ መጋራት” ስርዓት በአዲሱ ፖሊሲ ድጋፍ ማግኘቱን ተናግረዋል። በአዲሱ ፖሊሲ ላይ የተቀመጠው የውጪ መጋራት፤ በ2008 ዓ.ም. በወጣው “የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አዋጅ” ላይም ተጠቅሷል።
ይህ አዋጅ የፌደራል መንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት ሰልጣኞች፤ “ከስልጠና፣ ምዘና፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ተያያዥነት ላላቸው ጉዳዮች” ወጪዎችን እንዲጋሩ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ደንግጓል። የወጪ መጋራት ስርዓት በቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት ውስጥ የነበረ መሆኑን የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ አስታውሰዋል። ሆኖም ስርዓቱ “ያንን ያህል ቆንጣጭ ወይም ጫና የነበረው” እንዳልነበር ገልጸዋል።

“የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሰልጣኞች በወጪ መጋራት ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል” የሚል አቅጣጫን የያዘው አዲሱ ፖሊሲ፤ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ መሰረት መጣሉ ተገልጿል። በዚህም መሰረት ሰልጣኞችን በስርዓቱ ውስጥ በማስገባት፤ ተቋማቱ ወጪያቸውን የሚሸፍኑበት መንገድ እንደሚዘረጋ ተጠቁሟል። ስርዓቱን በምን መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እንደታቀደ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ተሻለ “በአንድ ጊዜ ዜጎች ላይ ትልቅ ሸክም የሚጭን ሳይሆን፤ በትንሽ በትንሹ የዜጎችን የመክፈል አቅም ታሳቢ ባደረገ መንገድ እየተተገበረ የሚቀጥል ነው የሚሆነው” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)