የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ሰኞ ጥር 13፤ 2016 መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ ሲጠናቀቅ፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንደሚቀጥል ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አርባ አምስት አባላት ያሉት የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚወያየው “በአበይት ሀገራዊ ጉዳዮች እና በልዩ ልዩ የፓርቲ አጀንዳዎች ላይ” እንደሆነ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል። በዛሬው ስብሰባ፤ ሁለቱ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ተቀምጠው ስብሰባ ሲመሩ ታይተዋል።
በመጋቢት 2014 የጸደቀው የብልጽግና ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፤ የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በሶስት ወር አንድ ጊዜ እንደሚያደርግ ይደነግጋል። የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በበኩሉ መደበኛ ስብሰባውን በየስድስት ወሩ የሚያደርግ መሆኑ በመተዳደሪያ ደንቡ ሰፍሯል።
ማዕከላዊ ኮሚቴው፤ የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴን ሪፖርትን የማዳመጥ፣ የመገምገም እና ውሳኔ በሚሹ ነጥቦች ላይ የመወሰን ኃላፊነት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ተሰጥቶታል። በፓርቲው ፕሬዝዳንት የተፈጸመን የስምምነት የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ የማጽደቅ ስልጣንን መተዳደሪያ ደንቡ የሰጠው ለማዕከላዊ ኮሚቴው ነው።
ለመደበኛ ስብሰባ ጥሪ የደረሳቸው የብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፤ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሲጎበኙ መዋላቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ብልጽግና ፓርቲ ያሉት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ብዛት 225 ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)