የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የዶ/ር ካሳ ተሻገርን ያለመከሰስ መብት አነሳ 

በተስፋለም ወልደየስ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 16፤ 2016 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ፤ የየካ ምርጫ ክልል ተወካይ የሆኑትን የዶ/ር ካሳ ተሻገርን ያለመከሰስ መብት አነሳ። የዶ/ር ካሳ የህግ ከለላ የተነሳው፤ “በአማራ ክልል ተደራጅቶ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ይንቀሳቀሳል” ከተባለ “ጸረ ሰላም ኃይል” ጋር “ትስስር ያላቸው” እና “ለቡድኑ መመሪያ ይሰጡ የነበረ በመሆኑ ነው” ተብሏል። 

የዶ/ር ካሳ ያለመከሰስ መብት መነሳት፤ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተመሳሳይ ውሳኔ የተላለፈባቸውን የክልል እና የከተማ ምክር ቤት ተመራጮችን ቁጥር ሶስት አድርሶታል። የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉን ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ጥያቄ ያቀረበው፤ የፍትሕ ሚኒስቴር እንደሆነ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር ተናግረዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ያቀረበውን ጥያቄ እንዲመረምር፤ ጉዳዩ ለከተማይቱ ምክር ቤቱ የሰላም፣ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተመራው ከአምስት ቀናት በፊት እንደሆነ በዛሬው ጉባኤ ላይ ተነግሯል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ለምክር ቤት አባላት እንደገለጹት፤ ኮሚቴው በእነዚህ ቀናት “ለወንጀል ጥርጣሬ የሚያበቃ አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን እና አለመኖራቸውን” ሲያጣራ ቆይቷል።


ቋሚ ኮሚቴው በዚህ የማጣራት ሂደቱ፤ ፍትሕ ሚኒስቴር ከላከው ደብዳቤ ባሻገር፤ በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር ካሳ ተሻገር የተጠረጠሩበትን የወንጀል ምርመራ መዝገብ መመልከቱን አቶ ሙሉነህ አስረድተዋል። ይህንኑ መዝገብ ለያዘው ዐቃቤ ህግ በቀረበ ጥያቄም፤ ተጨማሪ ሶስት ገጽ ማብራሪያ ለቋሚ ኮሚቴው እንደቀረበለትም ሰብሳቢው አብራርተዋል።  

“የምክር ቤት አባሉ የተከበሩ ዶ/ር ካሳ ተሻገር የተጠረጠሩበት ወንጀል በአጭሩ የሚያሳየው፤ ተጠርጣሪው በአማራ ክልል ተደራጅቶ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የሚንቀሳቀስ ጸረ ሰላም ኃይል ጋር ትስስር እንዳላቸው እና ለዚህ ቡድን መመሪያ የሚሰጡ የነበረ መሆኑን፤ ፍትሕ ሚኒስቴር የላከው ደብዳቤ፣ የምርመራ መዝገባቸው እና የተላከው ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያ ያሳያል” ሲሉ አቶ ሙሉነህ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።  

“ተጠርጣሪው የምክር ቤት አባል የጸረ ሰላም ኃይል በማደራጀት፣ ይኸ ኃይል በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲያደርስ፣ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ እና የኃይል ተግባሩ ስኬት እንዲያገኝ ቅሰቀሳ ሲያደርጉ እንደነበረ የቀረቡት መረጃዎች ያሳያሉ። ጽፈዋቸዋል የተባሉትን ሰነዶችን እና በፌስቡክ የለጠፏቸውን ማስረጃ ኮሚቴው ማየት ችሏል። በተለይም ተጠርጣሪው የጸረ ሰላም ኃይሉ የመሰባሰቢያ እና የስትራቴጂ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ፣ የስትራቴጂክ ሰነዶችን አፈጻጸም ላይ ምክር ሲሰጡ እና እንዲፈጸም ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን ማስረጃዎች በምርመራ ሰነዱ ላይ ቀርበዋል” ብለዋል የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ። 

ዶ/ር ካሳ “ፈጽመውታል” የተባለው ድርጊት፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል በወጣው አዋጅ እና በወንጀል ህግ መሰረት “የሚያስከስስ ከባድ ወንጀል” መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው መረዳቱን በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል። በዚህ መሰረት የዶ/ር ካሳን ያለመከሰስ መብት መነሳቱን በተመለከተ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እንዲያጸድቅ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አቅርቧል። ይህንን ውሳኔ ሃሳብ 91 የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት የደገፉት ሲሆን፤ ሁለት ተወካዮች ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።  

ዶ/ር ካሳ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትን የተቀላቀሉት፤ በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ነው። እኚሁ የገዢው ፓርቲ የምክር ቤት ተወካይ፤ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ላለፉት አምስት ወራት በእስር ላይ ቆይተዋል። የፌደራል ፖሊስ ዶ/ር ካሳን በቁጥጥር ስር ያዋለው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ባሳለፈበት ዕለት ሐምሌ 28፤ 2015 ነው።

ፖሊስ የምክር ቤት አባሉን የያዘው፤ “ለጥያቄ እፈልጋቸዋለሁ” የሚል ምክንያት በማቅረብ እንደሆነ ጠበቃቸው በወቅቱ ገልጸው ነበር። ሆኖም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በነሐሴ ወር መጀመሪያ በሰጠው መግለጫ፤ ዶ/ር ካሳን ጨምሮ 23 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ “በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ለማባባስ ህገወጥ ተግባራትን በመፈጸም” ተጠርጥረው መሆኑን አስታውቋል።


ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ “የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው” በሚል ከወነጀላቸው ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ይገኙበታል። ተጠርጣሪዎቹ “አስፈላጊው መረጃ ከተሰበሰበ” በኋላ “ወደ ፍትህ እንደሚቀርቡ” ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ በወቅቱ ቢያስታውቅም፤ ላለፉት ስድስት ወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ዶ/ር ካሳን ጨምሮ የተወሰኑት ተጠርጣሪዎች፤ በአፋር ክልል ወደሚገኘው አዋሽ አርባ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ተወስደው እስካለፈው ወር ድረስ በዚያ እንዲቆዩ ተደርገዋል። ዶ/ር ካሳ እና ጋዜጠኛ በቃሉ ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋወሩ የተደረገው፤ ህክምናቸውን በፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል እንዲከታተሉ ነበር።

እንደ ሁለቱ ተጠርጣሪዎቹ ሁሉ በአዋሽ አርባ ለወራት የቆዩት የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ ቧያለው፤ በተመሳሳይ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ከተዘዋወሩ አንድ ወር ሊሞላቸው ተቃርቧል። ሁለቱ የምክር ቤት አባላት ቀድመዋቸው አዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከተዘዋወሩት፤ ዶ/ር ካሳ ጋር በአንድ ክፍል እንዲታሰሩ መደረጉን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። እነዚህን የምክር ቤት አባላት፤ ከሶስት ሳምንት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ እንደተቀላቀሏቸውም ምንጮቹ ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል። 

ከእነዚህ የህዝብ ተወካዮች ውስጥ፤ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ያለመከሰስ መብት በዛሬው ዕለት ተነስቷል። ከትላንት በስቲያ ሐሙስ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤትም፤ የአቶ ዮሐንስ ቧያለውን ያለመከሰስ መብት በተመሳሳይ መልኩ ማንሳቱ ይታወሳል። የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) ባለፈው ሰኞ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው፤ የምክር ቤቱ አባል በሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)