የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን የተመለከተ “ስትራቴጂካዊ ግምገማ” ማካሄድ ጀመረ 

የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 2፤ 2016 “ስትራቴጂካዊ ግምገማ’’ ማካሄድ ጀመረ። የዛሬው ግምገማ፤ የሰላም ሂደቱ “ወሳኝ ሁኔታዎች” በተባሉት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፣ የትጥቅ መፍታት፣ ታጣቂዎች እንዲበተኑ ማድረግ እና ከህብረተሰቡ ጋር መልሶ ማዋሃድ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ጸጥታ ዲፓርትመንት ገልጿል።

የዛሬውን ግምገማ በንግግር የከፈቱት የአፍሪካ ህብረት ሙሳ ፋኪ ማህማት ናቸው። በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ሲደረግ የነበረውን የሰላም ንግግር የመምራት ኃላፊነት ሲወጡ የቆዩት፤ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆም በግምገማው መክፈቻ ላይ ንግግር አሰምተዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው የዛሬው መርሃ ግብር ዝርዝር፤ የፌደራል መንግስት፣ የህወሓት፣ የደቡብ አፍሪካ መንግስት እና የታዛቢዎች ተወካዮች በመክፈቻው ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። 

ፎቶዎች፦ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ጸጥታ ዲፓርትመንት

የፌደራል መንግስትን በመወከል በዛሬው ግምገማ ከተኙት ውስጥ በቅርቡ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ ይገኙበታል። በህወሓት በኩል የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ እንዲሁም በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ተገኝተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)