የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፒያሳ ለሚነሱ የግል አልሚዎች “ካሳ እና ምትክ መሬት” እንደሚሰጥ አስታወቀ 

በተስፋለም ወልደየስ

በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ከተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ጎን በሚገኘው ቦታ ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች፤ ከስፍራው እንደሚነሱ የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አበቤ ማረጋገጫ ሰጡ። ለእነዚህ የልማት ተነሺዎች የከተማው አስተዳደር “የጋራ መኖሪያ ቤት” አሊያም “አዲስ የሚገነባ የቀበሌ ቤት” እንደ የምርጫቸው እንደሚያቀርብ፤ በአካባቢው በተዘጋጀው ፕላን መሰረት ግንባታ ለማከናወን የገንዘብ አቅም ለሌላቸው የግል አልሚዎች ደግሞ “ካሳ እና ምትክ መሬት” እንደሚሰጥ ገልጸዋል። 

አዳነች ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኙ “የመንገድ ኮሪደር ልማት” ስራዎችን በተመለከተ በሰጡት ገለጻ ነው። በመንግስት እና ለመንግስት ቅርበት ባላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በትላንትናው ዕለት በተላለፈው በዚህ ገለጻ፤ የኮሪደር ልማቱን የተመለከተ ጥናት ሲከናወን የቆየው ከግንቦት 2015 ጀምሮ መሆኑ ተጠቅሷል። 

“ጨረታ ባሸነፉ የውጭ ባለሙያዎች” እንደተካሄደ የተነገረለት ይህ ጥናት፤ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች የተሰሩ የልማት ስራዎችን በማገናኘት “የከተማዋን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዴት ከፍ ማድረግ ይቻላል?” በሚል ዓላማ የተካሄደ መሆኑን ከንቲባዋ ተናግረዋል። የልማት ስራዎቹን የማገናኘት ስራ፤ የአዲስ አበባን “የቱሪዝም መስህብነቷን ሊጨምር በሚችል ደረጃ” እንደዚሁም የከተማይቱን “ሙሉ ውበት እና አገልግሎት” በያዘ መልኩ እንዴት ለጥቅም ሊውል እንደሚችል በጥናቱ መፈተሹንም አዳነች አስረድተዋል።

በዚህ መሰረት ሲካሄድ የቆየው ጥናት፤ ባለፉት ወራት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተያየት ሲሰጥበት ከቆየ በኋላ መጽደቁን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል። የአዲስ አበባን “አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን እና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሳድግ የሚችል” የተባለለት “የመንገድ ኮሪደር ልማት” በከተማዋ ካቢኔ የጸደቀው የዛሬ ሁለት ሳምንት የካቲት 15፤ 2016 ነበር።

በዚህ ፕሮጀክት እንዲለሙ ዕቅድ የተያዘላቸው አራት የመንገድ ኮሪደሮች፤ “ሁለንተናዊ የመንገድ ዘመናዊነት ያሟሉ ከመሆናቸውም በላይ ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማችንን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው” ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። አዲስ አበባ “የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚመጥን” ልማት ይካሄድባቸዋል ከተባሉ ከእነዚህ ኮሪደሮች መካከል ረጅሙ 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው። ይህ ኮሪደር ከፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ ተነስቶ በለገሃር፣ ሜክሲኮ፣ በሳርቤት በኩል እስከ ወሎ ሰፈር ያለውን መንገድ የሚያካልል ነው። 

እንደዚህኛው ሁሉ ከፒያሳ ጋር የሚገናኘው ሌላኛው ኮሪደር፤ ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ በአራት ኪሎ በኩል እስከ አድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ ድረስ ያለውን 6.4 ኪሎ ሜትር መንገድ የሚሸፍን ነው። በመንገድ ኮሪደር ልማት የተካተተው ሶስተኛ መንገድ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ ከአራት ኪሎ በመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ ድረስ የተዘረጋ ነው። በዚህ ፕሮጀክት ከተካተቱ በርዝመት አነስተኛው የሆነው፤ ከቦሌ አየር መንገድ እስከ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ ድረስ ያለው 4.9 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው።

በእነዚህ የመንገድ ኮሪደር ቦታዎች ላይ “ደረጃቸውን የጠበቁ ተሸጋጋሪ ድልድዮች፣ ማሳለጫዎች እና ሰፋፊ መጋቢ መንገዶች” እንደሚገነቡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የመንገድ ኮሪደር ፕሮጀክቶቹ “አዋሳኝ የወንዝ ተፋሰሶችን ያቀፉ፣ የሳይክልና ሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ የከተማዋን ማስተር ፕላን እና urban ዲዛይን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሁም ለከተማዋ እጅግ ዘመናዊ የትራንስፖርት ፍሰት የሚያጎናጽፉ መሆኑ እንደታመነበት” የዛሬ ሁለት ሳምንት በጽህፈት ቤቱ  በወጣው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።  

“የከተማ አረንጓዴ ልማትን ያካተተ” የተባለለት ይህ የመንገድ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከጸደቀ ማግስት ጀምሮ “ወደ ስራ እንዲገባ እና ልዩ ክትትል እንዲደረግለት” ውሳኔ ተላልፎ ነበር። ከንቲባ አዳነች በትላንትናው ዕለት በቴሌቪዥን በተላለፈ ገለጻቸው ይህንኑ አረጋግጠዋል። የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ኮሪደር ልማትን በወራት ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ “ለሊት እና ቀን” እየሰራ እንደሚገኝም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

“ይሄንን በምንሰራበት ሰዓት ከመንገድ ላይ የሚነሱ፣ ከመንገድ ላይ ወደ ውስጥ ጠጋ የሚሉ አጥሮች ይኖራሉ። ከተለያየ ቦታ ላይ በእርጅና አሁን ያለንበትን ዘመን የማይመጥኑ ግንባታዎች አሉ። ከከተማው መዋቅራዊ ፕላን ውጪ የተገነቡ አሉ። የተለያዩ ጥፋቶች አሉ። ከተማውን ለጎርፍ ሊዳርግ ይችላል። አጠቃላይ የፍሳሽ መስመሯን፣ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን ውጤታማ እንዳይሆን ሊያደርግ የሚችል መስተካከል ያለበት አለ። እርሱን ለማስተካከል ሰዎችን ከቦታቸው ልናነሳ እንችላለን” ሲሉም አዳነች ተናግረዋል። 

ከሚኖሩበት ቦታ ከሚነሱት ውስጥ በከንቲባዋ ገለጻ በምሳሌነት የተጠቀሱት፤ በአድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ናቸው። “የአድዋ ድል መታሰቢያ አበባ መስሎ፤ የውጭዎቹም፣ የሀገር ውስጦቹም መጥተው የሚጎበኙት እና የሚውሉበት ስፍራ ሆኗል። ወደ ጎን ደግሞ በምናይበት ሰዓት የማይመጥን ገጽታ አለ። ያንን መቀየር፣ አብሮ ሙሉ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉም ነዋሪዎቹ ከቦታው ላይ የሚነሱበትን ምክንያት አስረድተዋል። 

ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰዎችን ከመኖሪያቸው በሚያነሳበት ወቅት፤ ልማቱ “የሰው ህይወትን ጭምር አብሮ የሚያለማ” እንዲሁም ለህዝቡ “የተሻለ አኗኗርን ይዞ የሚመጣ መሆን አለበት” የሚለውን ታሳቢ እንደሚያደርግ አዳነች ተናግረዋል። “ሰው ተኮር ነን። [ልማት የምናካሄደው] ሰውን ማዕከል አድርገን ነው። ልማትን ከሰው ህይወት ነጥለን አንመለከትም” ሲሉ አጽንኦት የሰጡት ከንቲባዋ፤ በዚህም ምክንያት ከአድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ ለሚነሱ ነዋሪዎች “ቅድሚያ የት ነው የሚያርፉት የሚለውን እያሰብን ነው” ብለዋል።   

“የጋራ መኖሪያ ቤት የመረጡትን የጋራ መኖሪያ ቤት፣ የቀበሌ ቤት የመረጡትን እንደ ድሮው በጭቃ ቤት ሳይሆን አዲስ ፎቆች [እንገነባለን]። መጸደጃ ቤት ያላቸውን፣ ማብሰያ ቤት ያላቸውን፣ ለመኖር ምቹ የሆኑ የጋራ መገልገያ ስፍራዎች ጭምር ያሏቸው፣ ጥሩ ንጹህ ቤቶች ሰርተን፤ ከዚህ ከተለባበዱ፣ እየወደቁ ካሉ እና እየፈራረሱ ካሉ ቤቶች ውስጥ ህዝባችንን፣ ነዋሪዎቻችንን አክብረን እያወጣን፤ ቃላችንን ጠብቀን በዚህ ሁኔታ ነው የምናስተናግደው” ሲሉም አዳነች አብራርተዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእዚህ አካባቢ ለመገንባት በጥናት ያዘጋጀውን “ፕላን” ጠብቀው መስራት ለሚፈልጉ “የግል አልሚዎች” ቅድሚያ እንደሚሰጥም ከንቲባዋ ተናግረዋል። የግል አልሚዎቹ ግንባታውን ለማከናወን የገንዘብ አቅም ከሌላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ “ካሳ እና ምትክ መሬት” እንደሚሰጥ አዳነች ገልጸዋል። “የሚነሱበትን አካባቢ ማዕከል ያደረገ፤ ከመሃል ከተማ ከሆነ መሃል ከተማ አካባቢ ቦታ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ነው የምንሰራው” ሲሉም ከንቲባዋ አክለዋል።

የመንገድ ኮሪደር ልማቱ በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ “ትዕግስት በማድረግ”፣ “ልማቱን በመደገፍ”፣ ፈጠን ፈጠን ብሎ በመነሳት” እንዲሁም “መንገድ መልቀቅ በሚያስፈልግበት ቦታ ላይ መንገድ በመልቀቅ” በትብብር በጋራ እንዲሰራ አዳነች በገለጻቸው ማጠቃለያ ጥሪ አቅርበዋል። “ህዝባችን በጣም ይረዳናል ብለን ነው የምናስበው። እየተረዳ እንደሆነም አይተናል። በተለይ የአድዋ ድል መታሰቢያ ይህንን እውን አድርጓል” ሲሉም ተደምጠዋል። 

እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ የመንገድ ልማት ኮሪደሩ በሚያልፍባቸው ቦታዎች ከመኖሪያ ስፍራቸው እንዲለቀቁ የተነገራቸው ነዋሪዎች ዘንድ ያለው ስሜት ግን በተቃራኒው ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ቀበና አካባቢ በተለምዶ ቢሻን ጋሪ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ዋናው መንገድ ዳር ያሉ ነዋሪዎች፤ “በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አካባቢውን ልቀቁ መባላቸው” ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ሰራተኞች “ስለ አካባቢ ልማት” ለሚደረግ ውይይት ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 23፤ 2016 የስብሰባ ጥሪ ደብዳቤ እንደሰጧቸው ነዋሪዎቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከል በማግስቱ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ የክፍለ ከተማው ኃላፊዎች መገኘታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። 

በስብሰባው ላይም ነዋሪዎቹ “ ‘ልማት ለምን ይለማል?’ የሚል ጥያቄ እንደሌላቸው ነገር ግን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ትለቃላችሁ መባላቸው ቅር እንዳሰኛቸው” መናገራቸውን ጠቅሰዋል። በአንድ ወር ጊዜ ወስጥ እንዲነሱ የተነገራቸው፤ በቀበና አካባቢ ከሀቤት ህንፃ እስከ ሊዲያ ካፌ ድረስ ባለው ዋናው መንገድ ዳር ያሉ 36 ቤቶች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የተቀሩት ቤቶች ደግሞ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚነሱ የክፍለ ከተማው ሰራተኞች ለነዋሪዎቹ እንደነገሯቸውም አክለዋል።

ከቀበና ወንዝ መቶ ሜትር ርቀት ላይ በግራም በቀኝም ያሉ ቤቶች፤ “በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ትነሳላችሁ” መባላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በእሁዱ ስብሰባ የተገኙ የየካ ክፍለ ከተማ ኃላፊዎች፤ አካባቢው ለልማት ስለሚፈለግ “ሁለም የመንደሩ ነዋሪ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ” ማሳሰቢያ ሰጥተዋል ተብሏል። በዚህም መሰረት በቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች “ውል እንዲያድሱ”፤ የግል ባለይዞታዎች ደግሞ የ2016 ዓ.ም. ግብር የተከፈልበትን ወረቀት እንዲሁም የቤቱን ካርታ ይዘው እንዲጠብቁ እንደተነገራቸው ነዋሪዎቹ ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ለዚህ ዘገባ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ናሆም አየለ አስተዋጽኦ አድርጓል]