የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ለህክምና ወደ ውጭ ሀገራት የሚያደርጉት ጉዞ ከአሁን በኋላ “እንደማይፈቀድ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። የስራ ኃላፊዎቹ በውጭ ሀገራት ያሏቸውን የህክምና ቀጠሮዎች ከዛሬ ጀምሮ በመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲያካሄዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዝዘዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፤ በቢሾፍቱ ከተማ የተገነባውን የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 10፤ 2016 በመረቁበት ወቅት ባሰሙት ንግግር ነው። መሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠለተ ከ35 ዓመት በኋላ መመረቁ የተነገረለት ይህ ሆስፒታል፤ የኩላሊት እጥበት፣ የነርቭ፣ የሳምባ እና መተንፈሻ አካላትን ጨምሮ ሌሎችንም የህክምና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው።
ዘመናዊ የሆኑ የአጥንት ምርመራ ማዕከል፣ የሞሎኪዩላር ላብራቶሪ፣ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ክፍል ያሉት ይህን ሆስፒታል፤ በ76 ሺህ ካሬ ሜትር አጠቃላይ የመሬት ይዞታ ያለው ነው። የሆስፒታሉ ህንጻ ያረፈበት የመሬት ስፋት ብቻውን 29 ሺህ ካሬ ሜትር መሆኑን ከኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የምረቃ ንግግራቸው፤ የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ለግንባታ በፈጀው ጊዜ እና በዘመናዊነቱ “ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሆስፒታሎች ይለያል” ብለዋል። “በዚህ ጥራት፣ በዚህ ስፋት፣ በዚህ የቴክኖሎጂ አቅም የተሰራ ሆስፒታል ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሌለ፤ በሀገራችን ደረጃ አሁን ባለው ሁኔታ አንደኛው ሆስፒታል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል” ሲሉም አብይ ተናግረዋል።
አብይ “ድንቅ ሆኖ የተሰራ” ሲሉ የጠሩትን ይህን ሆስፒታል፤ በውጭ ሀገራት የህክምና ክትትል የሚያደርጉ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ሊገለገሉበት እንደሚገባ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። “ከእንግዲህ በኋላ ወደተለያዩ ሀገራት ለህክምና የሚሄዱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፤ የህክምና ቦታቸው ቢሾፍቱ መሆኑን ከዛሬ ጀምሮ እንዲያውቁ አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።
“ማንኛውም የውጭ ሀገር የህክምና ቀጠሮ” ያላቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ክትትላቸውን በመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲያደርጉ ያዘዙት አብይ፤ ከዚህ ሆስፒታል ውጪ የውጭ ሀገር የህክምና ጉዞ ከዚህ በኋላ “እንደማይፈቀድ” አስታውቀዋል። ይህንንም የጤና ሚኒስቴር እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዲያስፈጽሙ መመሪያ ሰጥተዋል።

አብይ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት “እኛ ሰርተን፣ እኛ የማንገለገልበት ከሆነ፤ እኛ ሰርተን እኛ ያላከበርነው ከሆነ ሌላው ስለማይጠቀምበት [ነው]” በሚል ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። ከመንግስት ባለስልጣናት ውጪ ባለው የህብረተሰብ ክፍል ጭምር ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር በሚደረግ ጉዞ “ከፍተኛ ሀብት እንደሚወጣ” የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የህክምና ችግር ያለባቸው ሰዎች ዛሬ የተመረቀውን ሆስፒታል “እንዲያዩ” እና “እንዲገለገሉበት” ጋብዘዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የጤና ፖሊሲ “በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ” እንደሆነ ያስታወሱት አብይ፤ ፖሊሲው እንደተጠበቀ ሆኖ “ታማሚ ካለም፤ የማከም ብቃት መፈጠር አለበት” በሚል ሀሳብ “በርከት ያሉ” ሆስፒታሎች እየተገነቡ መሆኑን ጠቁመዋል። “ ‘ሰዎች የመከላከል ሙከራዎቻችን አልፈው ሲታመሙ የማከም ብቃት መገንባት አለብን’ በሚል እሳቤ፤ አዲስ አበባ ውስጥም በርከት ያሉ አዳዲስ ሆስፒታሎች ተጀምረዋል። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ጸዳ፣ ጸዳ ያሉ ሆስፒታሎች እንደሚኖሩን ይጠበቃል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)