የአዲስ አበባ ከተማ የ2017 በጀት የሚጸድቅበት መደበኛ የምክር ቤት ጉባኤ ነገ ይጀመራል 

በቤርሳቤህ ገብረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ነገ ረቡዕ ሐምሌ 10፤ 2016 እና በቀጣዩ ቀን በሚያካሄደው መደበኛ ጉባኤ፤ ለከተማይቱ አስተዳደር የተመደበውን የ2017 በጀት ሊያጸድቅ ነው። በዚህ ጉባኤ ላይ የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የበጀት ዓመቱን ማጠቃለያ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በ1995 ዓ.ም በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር መሰረት፤ የከተማው ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ የሚገባው በየሁለት ወሩ ነው። ምክር ቤቱ የመጨረሻውን ጉባኤውን ያደረገው ባለፈው ሚያዝያ ወር ሲሆን በዚህ ስብሰባውም 21.7 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቆ ነበር። 

ከዚህ ተጨማሪ በጀት ውስጥ 96 በመቶ የሚሆነው ተመድቦ የነበረው፤ “ለተጀመሩ የግንባታሥራዎች፣ ለመንገድ፣ ለካሳ ክፍያ፣ ለአረንጓዴ ልማት እና አካባቢ ጥበቃ ስራዎች ማጠናቀቂያ እንዲሁም ለጤና ተቋማት የውስጥ ግብዓት ማሟያ” መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። 

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በነገው ዕለት በሚጀምረው መደበኛው ጉባኤው፤ ለከተማ አስተዳደሩ የተመደበ 230 ቢሊየን ብር በጀት በተመሳሳይ መልኩ ያጸድቃል ተብሎ ይጠብቃል። ይህ በጀት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ42 በመቶ እድገት ያለው ነው።

የ2017 በጀት ረቂቅ ሰነድ በምክር ቤቱ መደበኛው ጉባኤ ላይ ከመቅረቡ አንድ ሳምንት አስቀድሞ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው “ባለድርሻ አካላት” ውይይት አድርገውበት እንደነበር ተገልጿል። በምክር ቤቱ የመንግስት በጀት፣ ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው በዚሁ ውይይት ላይ፤ ከ2017 ረቂቅ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው “ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል የካፒታል በጀት” መሆኑ ተነግሯል። 

ረቂቅ በጀቱ ለትምህርት፣ ለውሃ፣ ለመንገድ፣ ለትራንስፖርት፣ ለጤና እና ለሌሎችም ፕሮጀክቶች “ልዩ ትኩረት” እንደሰጠም በዚሁ ውይይት ላይ ተነስቷል። ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ከበጀት በተጨማሪ የከተማይቱ ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርትም ይቀርባል ተብሏል። 

የከተማይቱ ምክር ቤት ሰባት ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ያደረጓቸውን የመስክ ምልከታዎችን እና ክትትሎችን መሰረት  አድርገው ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉ ተጠሪ ተቋማት የሚሰጡት ማብራሪያም በሁለቱ ቀናት መደበኛ ጉባኤ ይጠበቃል።  

“ኢትዮጵያን ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል፤ ከአስፈጻሚ አካላት አመታዊ ሪፖርት እና ረቂቅ በጀት በተጨማሪ የምክር ቤቱ የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ረቂቅ ቀርቦ ይጸድቃል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ነገ እና ከነገ በስቲያ የሚያደርጉት ጉባኤ፤ በዓመቱ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)