በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር “ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን” ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ

በሙሉጌታ በላይ

መንግስታዊው የቴሌኮም  አቅራቢ ተቋም ኢትዮ ቴሌኮም፤ በአማራ ክልል የተቋረጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት ለሁሉም ደንበኞች መልሶ ለማስጀመር፤ ከክልሉ መንግስት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታወቀ። በክልሉ ያሉ የተለያዩ ተቋማት የኢንተርኔት አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ማግኘት መጀመራቸውን ተቋሙ ገልጿል።

ኢትዮ ቴሌኮም ይህን የገለጸው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተጠናቀቀውን 2016 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸምን በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 3፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። የዛሬውን መግለጫ ለሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፤ “በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠበትን” የአማራ ክልል የተመለከቱት ይገኙበታል።

በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ተቋሙ ያጣው ገቢ ምን ያህል እንደሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተጠይቀዋል። በዋነኛነት በአማራ ክልል ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ፤ በክልሉ ተቋርጦ የቆየው የኢንተርኔት አገልግሎት “የሚመለስበት ዕድል አለ ወይ?” የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸዋል።

ፎቶ፦ ኢትዮ ቴሌኮም

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የወሰነው ሐምሌ 28፤ 2015 ነበር። ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው በክልሉ እየተካሄደ ነው ያለውን “በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ”፤ “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ መሸጋገሩን” በመግለጽ ነበር። ይህ ውሳኔ ከመተላለፉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፤ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉም ይታወሳል።

በአማራ ክልል የሚገኙ፣ “ኢኮኖሚውን ለማሳለጥ የሚያስፈልጉ” የተባሉ ተቋማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት እያገኙ ያሉት ተቋማት “መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ኢንተርፕራይዞች” እንደሆኑ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በክልሉ የተቋረጠውን የኢንተርኔት አገልግሎት “በዘለቄታዊነት ለመፍታት” ጥረት እያደረገ መሆኑን ፍሬሕይወት አስታውቀዋል። ይህንኑ በተመለከተም ተቋማቸው “ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር” እየተነጋገረ መሆኑንም አስረድተዋል። 

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ “ባለድርሻ” ሲሉ ከጠሯቸው አካላት ውስጥ “የኢንተርኔት መዘጋቱ ከሚመለከተው ተቋም” እና የአማራ ክልል መንግስትን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። “በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ለሁሉም ደንበኛ ኢንተርኔቱ እንደሚከፈት ነው ተስፋ የምናደርገው” ሲሉም አገልግሎቱን በቅርቡ መልሶ ለማስጀመር የሚቻልበት ዕድል እንዳለም ጠቁመዋል።

ፍሬሕይወት በአማራ ክልል የኢንተርኔት የአገልግሎቱ መቋረጥ፤ በሚመሩት ተቋም “እድገት፣ እቅድ እና ገቢ” ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን አልሸሸጉም። ሆኖም ተቋሙ በዚህ ሳቢያ ያጣው ገቢ ምን ያህል እንደሆነ መግለጽ “ጠቃሚ አለመሆኑን” በማንሳት አሃዛዊ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። የኢንተርኔት መቋረጡ “በገቢ ላይ ምን ያህል ተጽእኖ ፈጠረ የሚለውን ለክተናል። ብዙ ጊዜ ይህን ቁጥር ከመስጠት የምንቆጠብበት ምክንያት ምንም value አይጨምርም በማለት [ነው]” ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“የያዝነውን እቅድ ለማሳካት፤ ዓመቱን ሙሉ ሌሎች ብዙ አማራጮችን ስንሰራ ነው የቆየነው። በጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅ፤ ያን ሁሉ ተግዳሮት አልፈን፣ ይሄንን አሳክተናል ብለን ነው [እየተናገርን ያለነው]። በአንድ ቦታ ላይ በተፈጠረው ‘ይሄን ያህል ገንዘብ አጥተናል’ ብለን ለማህበረሰባችን እና ለደንበኞቻንን አሉታዊ ነገር ማቅረብ አንፈልግም” ሲሉም ኢትዮ ቴሌኮም በኢንተርኔት መቋረጡ ያጣውን ገቢ መጠን መግለጽ ያልፈለጉበትን ምክንያት አብራርተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወር የስራ አፈጻጸሙን ባለፈው ጥር ወር ይፋ ባደረገበት ወቅትም፤ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ለቀረበላቸው ጥያቄ ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተው ነበር። በወቅቱ በጋዜጠኞች የቀረበው ጥያቄ፤ በአንድ ዓለም አቀፍ ሪፖርት ላይ የቀረበን አሃዝ ያጣቀሰ ነበር። 

ሪፖርቱ ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ላይ በጣለችው ገደብ ሳቢያ፤ በፈረንጆቹ 2023 ዓመት “1.59 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ ጥቅም አጥታለች” የሚል ነው። ሪፖርቱ “ቀጥታ ኢትዮ ቴሌኮምን የሚመለከት አይደለም” ያሉት ፍሬሕይወት፤ ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የኢንተርኔት መቋረጥ “ኢትዮ ቴሌኮም ላይ የዚያን ያህል የገቢ ተጽዕኖ አልተፈጠረም” ሲሉ በወቅቱ አስተባብለዋል። ሆኖም ተቋማቸው በዚህ ምክንያት ያጣውን የገቢ መጠን፤ በጥር ወሩ መግለጫቸውሳይገልጹ ቀርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)