በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች፤ የተማሪዎቻቸውን ምዝገባ “በኦንላይን” እንዲያካሄዱ ተደረገ 

በሙሉጌታ በላይ

በአዲስ አበባ ከተማ ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በሚያስተምሩ ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች፤ የ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባን “በኦንላይን” እንዲያካሄዱ ተደረገ። አዲሱ አሰራር በአዲስ አበባ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ በቀጣይ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ባወጣው የ2017 የትምህርት ዘመን የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ የነባር ተማሪዎች ምዝገባ እና የመጽሐፍት ስርጭት መከናወን የነበረበት ከሰኔ 24 እስከ ሰኔ 30፤ 2016 ዓ.ም ነበር። ሆኖም የመንግስት ትምህርት ቤቶች በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ባደረጉት የ“ኦንላይን ምዝገባ” ምክንያት፤ ሂደቱ ሰኔ 30 እንዲጀምር ተደርጎ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል።

የ“ኦንላይን ምዝገባው” በከተማይቱ በሚገኙ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል በሚያስተምሩ 555 የመንግስት ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ መሆኑን በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት እና ማስፋት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ዳኜ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአዲሱ አሰራር ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አቶ ደረጀ፤ በመጀመሪያው ሳምንት የምዝገባ ጊዜ ብቻ 16,000 ተማሪዎች መመዘገባቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ሲከናወን የቆየውን የወረቀት ምዝገባ ያስቀረው አዲሱ አሰራር፤ ተማሪዎች ኢንተርኔትን በመጠቀም ከየትኛውም ቦታ ሆነው “E-School system” በተባለ ሶፍትዌር አማካኝነት እንዲመዘገቡ የሚያደርግ ነው። ሶፍትዌሩ እንዲለማ የተደረገው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከከተማይቱ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ካደረጉት ጥናት በኋላ ነው።

ሁለቱ ቢሮዎች ያደረጉት ጥናት “አጠቃላይ የትምህርት መረጃ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ” ያለመ እንደነበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የከተማይቱ ትምህርት ቢሮ ሶፍትዌሩን ከማልማት ባሻገር ለሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮች፣ የአይ.ሲ.ቲ. ባለሙያዎች እና ተወካዮች በሰኔ ወር ስልጠና ተሰጥቷል።  

ከዚህ በተጨማሪም “የኦንላይን ምዝገባ መመሪያ” የተሰኘ በጽሁፍ የተዘጋጀ ሰነድ ለትምህርት ቤቶች አሰራጭቷል። ይህ መመሪያ፤ አንድ ተማሪ የ“ኦንላይን” ምዝገባውን ለመፈጸም የሚያስፈልጉትን ሰነዶችን እና የምዝገባ ሂደቱን የሚያብራራ ነው። በመመሪያው መሰረት አንድ ተማሪ ምዝገባውን ለማድረግ፤ ማንነቱን በሚገባ የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ፣ የልደት ሰርተፊኬት፣ የዓመቱን የውጤት ሪፖርት ካርድ ማሟላት ይጠበቅበታል። 

ወላጆች እና አሳዳጊዎችም በመመሪያው የተቀመጠውን አካሄድ ተከትለው የልጆቻቸውን ምዝገባ ማከናወን እንደሚችሉ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል። ይህን የሚያደርጉ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ፎቶግራፍ እና መታወቂያቸውን ማያያዝ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ መልኩ የሚከናወነው የ“ኦንላይን” ምዝገባ፤ የተማሪዎችን አጠቃላይ የትምህርት መረጃ ማግኘት የሚያስችል መሆኑን  ዶ/ር ዘላለም ያስረዳሉ።   

“አንድ ተማሪ አንደኛ ክፍል ሲገባ ወይም ሲጀምር ሙሉ መረጃ ይያዛል። ስንተኛ ክፍል በስንት ዓመቱ እንደገባ፣ በስንት ዓመት እንዳጠናቀቀ ሙሉ መረጃ ይይዛል። ስለዚህ [ስለተማሪው] ማወቅ ሲፈለግ፤ የት ክፍለ ከተማ ነው የተመዘገበው? ትምህርት ቤት ቀይሯል ወይ? ወድቋል ወይ? ውጤቱ ምን ይመስላል የሚለውን ዝርዝር ይነግርሃል” ሲሉ የትምህርት ቢሮው ኃላፊ የአዲሱን ሶፍትዌር ጠቀሜታ አብራርተዋል።

በመንግስት ትምህርት ቤቶች “በሙከራ ደረጃ” ተግባራዊ እየተደረገ ነው የተባለለት ይህ ሶፍትዌር፤ ከተማሪዎች የትምህርት መረጃ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሁሉንም  ትምህርት ቤቶች “ሙሉ መረጃ” እንደሚይዝ አቶ ደረጀ ገልጸዋል። እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ድረስ ይቆያል ተብሎ የተገመተው የመንግስት ትምህርት ቤቶች የ“ኦንላይን” ምዝገባ ሲጠናቀቅ፤ የግል ትምህርት ቤቶችም አዲሱን አሰራር ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንደሚደረግም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)