በክልሎች የሚደረገው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ በመጪው ሳምንት ሊጀመር ነው

በናሆም አየለ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በክልሎች የሚያደርገውን የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ፤ በቀጣዩ ሳምንት እንደሚጀምር ገለጸ። የምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚካሄድባቸው፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ናቸው።

በሀገራዊ ምክክር ላይ “አጀንዳ ሊሆኑ ይገባሉ” የተባሉ ጉዳዮች የማሰባሰብ ሂደት በቅድሚያ የተካሄደው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ነበር። ይህንኑ ሂደት በቀጣይነት በሶስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለማካሄድ የተወሰነው፤ አጀንዳ በማሰባሰብ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ አስቀድሞ ስለተጠናቀቀባቸው መሆኑን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ዘገየ አስፋው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሶስት ወር በፊት በሰጠው መግለጫ፤ ከሶስቱ ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በተጨማሪ የምክክር አጀንዳዎችን የሚለዩ ተወካዮች ምርጫ በአፋር፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች “ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቁን” አስታውቆ ነበር።

በየክልሎቹ የሚኖረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከተካሄደው ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ኮሚሽነር ዘገየ  ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚሁ ሂደት መሰረት፤ በየክልሉ ካሉ 10 የህብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ የወረዳ ተወካዮች ወደ ክልል ከተሞቹ እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ ተመካክረው አጀንዳዎቻቸውን እንዲለዩ ይደረጋል። እነዚህ ተወካዮች ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ቀጣይ ምክክር ያደርጋሉ።

“ከወረዳዎች ተወክለው የመጡት የህብረተሰብ ክፍሎች፤ በክልሉ ላይ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የየክልሉን አጀንዳዎች ይለያሉ። በዋናው ሀገራዊ ጉባኤ የሚወክሏቸውን ተወካዮችንም ይመርጣሉ” ሲሉ ኮሚሽነር ዘገየ ሂደቱን አስረድተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፤ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ቁጥራቸው ከሁለት ሺህ የሚልቅ ሰዎች መሳተፋቸው ይታወሳል። 

እነዚህ ተሳታፊዎች፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተፈናቃዮች፣ የተገለሉ ማህበረሰቦች እና የህብረተሰብ መሪዎችን የወከሉ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል። ለሰባት ቀናት በተካሄደው የአዲስ አበባው አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ለምክክር እንዲቀርቡ ከተመረጡ ጉዳዮች መካከል፤ የአዲስ አበባ ባለቤትነት እና አወቃቀር፣ የቋንቋ፣ የሰንደቅ አላማ እና የህገ መንግስት ጉዳዮች ይገኙበታል።

በሶስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ የሚደረገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፤ በስድስት ቀን ለመጨረስ መታቀዱን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ካሉት 11 ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት አቶ ዘገየ ገልጸዋል። ለዚሁ ሂደት ይረዳ ዘንድ፤ የኮሚሽኑን ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን በትላንትናው ዕለት ወደ አሶሳ ከተማ መጓዙን ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በሚካሄድባቸው ቦታዎች፤ ሁለት ወይንም ሶስት የሀገራዊ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች እንደሚገኙም ተነግሯል። የኮሚሽነሮቹ ዋና ተግባር በየክልሎቹ የሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ፤ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የአሰራር ስነስርዓት መሰረት መፈጸሙን  መከታተል ይሆናል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)