በናሆም አየለ
ከጣሊያን ወራሪ ሰራዊት ጋር ለተፋለሙ አርበኞች መታሰቢያ እንዲሆን በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የተገነባው የአርበኞች ህንጻ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትዕዛዝ እንዲፈርስ ተደረገ። ዘንድሮ 60 ዓመቱን የደፈነው ህንጻ እንዲፈርስ የተደረገው፤ ቦታው ለመንገድ ኮሪደር ልማት በመፈለጉ ምክንያት እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ከሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ይህ ህንጻ ንብረትነቱ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ነው። ማህበሩ “የዐርበኞች ግንብ” በሚል ስያሜ በ1956 ዓ.ም ከተገነባለት ከዚህ ህንጻ ጎን፤ ሌላ ባለ አራት ወለል ህንጻ ከ13 ዓመት በፊት አሰርቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።
የአርበኞች ማህበሩ ዋና ጽህፈት ቤቱን ወደ አዲሱ ህንጻ ካዛወረ በኋላ፤ የቀድሞውን ህንጻ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት በማከራየት ገቢ ሲያገኝ ቆይቷል። ከ800 በላይ አባላት ያሉት ይህ ማህበር፤ የአርበኝነት ትግሉን እና የታጋዮችን ታሪክ የሚዘክር ሙዚየም በህንጻው ውስጥ አዘጋጅቶ ለጉብኝት ክፍት አድርጎም ነበር።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በባለቤትነት ሲያስተዳድራቸው የቆያቸውን ሁለት ህንጻዎች ለቅቆ የወጣው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሐምሌ 3፤ 2016 እንደሆነ የማህበሩ ፕሬዝዳንት የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እዝራ ንጋቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የማህበሩን አንድ ህንጻ ተከራየቶ የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት፤ ከዚህ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ አገልግሎት ማቋረጡን ባወጣው ማስታወቂያ ይፋ አድርጓል።
ምድብ ችሎቱ በዚሁ ማስታወቂያው፤ የአድራሻ ለውጥ ለማድረግ የተገደደው “ቦታው ለኮሪደር ልማት የሚውል” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በጻፈው ደብዳቤም፤ ህንጻዎቹ የሚፈርሱት “ቦታው ለልማት በመፈለጉ” እንደሆነ መጥቀሱን አቶ እዝራ አስታውቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ደብዳቤውን ለማህበሩ የላከው ከሶስት ወራት በፊት ይሁን እንጂ ህንጻዎቹን የማፍረስ ሃሳብ አቶ ታከለ ኡማ ከንቲባ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ መሆኑን የጽህፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል። “ታከለ ኡማ አነሳዋለሁ ሲል ‘አርበኞችን ለማጥፍት ነው’ ተብሎ ከስልጣኑ ተነሳ። ከዚያ አይፈርስም ተብሎ ነበር። በመሀል ‘ለላይብረሪው አይመችም’ ተባለ። አብርሆት ላይብረሪን ይከልለዋል ነው’ የሚባል። [አሁን] ለአብርሆት ላይብረሪ ማስፋፊያ ነው የሚፈርሰው” ሲሉ አቶ እዝራ እቅዱ የቆየ እንደሆነ አብራርተዋል።

ስለ ጉዳዩ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃን ገብረጻዲቅ፤ “እኛ [ህንጻውን] እያፈረስን ያለነው ለኮሪደር ልማቱ ነው። ቦታው ለአብርሆት ቤተመጻህፍት ማስፋፊያ ይፈለግ፤ ሌላ ህንጻ ሊገነባበት የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በአንድ ጊዜ ከሁለት ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ የሚችለው አብርሆት ቤተመጻህፍት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከሁለት አመት ከመንፈቅ በፊት በታህሳስ 2014 ዓ.ም. ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሃሳብ አመንጪነት 1.1 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበት የተገነባው የአብርሆት ቤተመጻህፍት፤ አራት ወለሎች ያሉት ሲሆን 1.4 ሚሊየን መጻሐፍትን መያዝ ይችላል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው “የመንገድ ኮሪደር ልማት” የአብርሆት ቤተ መጻሐፍት አካባቢንም ያካለለ ነው። ከቀይ ባህር ኮንዶሚኒየም እስከ አብርሆት ቤተ መጻሐፍት ያለው መንገድ እንዲሁም ከቱሪስት ሆቴል በፖስታ ቤት አድርጎ ወደ አብርሆት ቤተ መጽሐፍት የሚወስደው መንገድ የኮሪደር ልማት የተከናወነባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከአብርሆት ቤተ መጻሐፍት አጠገብ የሚገኘው የአርበኞች ህንጻ እንደሚፈርስ፤ ለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አመራሮች የተነገራቸው “ከሶስት ወር በፊት” መሆኑን የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃን ይናገራሉ። “ተግባብተን ያደረግነው ነገር ነው” ሲሉ ሂደቱ በስምምነት የተከናወነ እንደሆነም ይገልጻሉ።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የማህበሩ ፕሬዝዳንት የጽህፈት ቤት ኃላፊ “ባይሆን ደስ ይለን ነበር” ሲሉ የህንጻዎቹ መፍረስ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በፈረሰው ህንጻ ምትክ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማህበሩ አዲስ ህንጻ ለመገንባት መወሰኑ ግን እርምጃውን በበጎ ጎኑ እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል።
ይህንኑ ውሳኔ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ አዲሱ የማህበሩ ህንጻ የሚገነባው በአራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አጠገብ በሚገኝ ቦታ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚሁ ህንጻ ይፋዊ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ ስርአት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በቅርቡ ይከናወናል ተብሏል።

አዲሱ ህንጻ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ፤ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ትምህርት ሚኒስቴር ጎን በሚገኝ ህንጻ ላይ በከተማ አስተዳደሩ አማካኝነት ጊዜያዊ ቢሮ እንደተሰጠው አቶ እዝራ ተናግረዋል። ማህበሩ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በአዲሱ ቢሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)