በቤርሳቤህ ገብረ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጋራ መኖሪያ (ኮንዶሚኒየም) ቤቶች ግንባታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰደውን 29.8 ቢሊዮን ብር ብድር “በአስቸኳይ” እንዲከፍል ቀነ ገደብ ተሰጠው። አስተዳደሩ ብድሩን በአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ጊዜ ውስጥ እንዲከፍል ቀነ ገደብ የሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ለከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 8፤ 2016 በጻፈው ደብዳቤ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚውል ብድር በተለያየ ጊዜ መስጠቱን ጠቅሷል። ባንኩ ለከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ብድሩን የሰጠው፤ የቦንድ ግዢ ዋስትና በመያዝ እንደሆነም “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው ደብዳቤ ላይ ሰፍሯል።
ሆኖም ኮርፖሬሽኑ የወሰደውን ብድር በተዋዋለበት ጊዜ ባለመመለሱ እና ውዝፍ ዕዳ በመጠራቀሙ፤ ወደ ባንኩ የተበላሸ ብድር መደብ ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ያትታል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ክትትል ክፍል ይህንንኑ በመጥቀስ፤ ገንዘብ ሚኒስቴር በሰጠው ዋስትና መሰረት ቀሪው ብድር እንዲከፈለው ጥያቄ ማቅረቡም በደብዳቤው ተመላክቷል።
ለገንዘብ ሚኒስቴር በግንቦት እና በሰኔ ወር የተላኩት ደብዳቤዎች፤ የብድሩ መጠን 29.8 ቢሊዮን ብር መሆኑን የጠቀሱ ናቸው። ባንኩ ከብድር ክፍያ ሊሰበሰብ ይገባ የነበረው ገንዘብ በወቅቱ ገቢ አለመደረጉ፤ መንግስት በእቅድ የያዛቸውን “ትልልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም” “አሉታዊ ተጽእኖ” እንደፈጠረ በገንዘብ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ፊርማ ለከተማ አስተዳደሩ የተላከው ደብዳቤ ያስገነዝባል።
ለከተማ አስተዳደሩ የተሰጠው ብድር “የተበላሸ መደብ” ውስጥ መግባቱ፤ በባንኩ እና በሀገር ላይ ተመሳሳይ ተጽእኖ መፍጠሩንም ደብዳቤው አጽንኦት ሰጥቷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን በመገንዘብ፤ ያለበትን ብድር እስከ ነሐሴ 30፤ 2016 “በአስቸኳይ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ እንዲያደርግ” ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ባቀረቡት የበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ሪፖርት፤ የከተማ አስተዳደሩ አሁን ያለበት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ብድር ወደ 32.7 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን አስታውቀው ነበር። የከተማ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለወሰደው የቦንድ ብድር በ2016 በጀት ዓመት የከፈለው 16 ቢሊዮን ብር መሆኑንም ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በ2015 በጀት ዓመትም 22.5 ቢሊዮን ብር ለተመሳሳይ አላማ መክፈሉን አስታውቆ ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ በግንባታ ላይ የነበሩ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሳይጠናቀቁ በመቆየታቸው ምክንያት፤ የተጠራቀመው ብድር 54 ቢሊዮን ብር መድረሱ ከሁለት አመት በፊት ተገልጾ ነበር።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ወራት ላይ ለከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ ብድር መስጠትን አቁሞ እንደነበር ይታወሳል። ከወራት በኋላ መንግስታዊው ባንክ እና የከተማ አስተዳደሩ በጋራ ባደረጉት ግምገማ፤ ብድሩን መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረው ስምምነት ላይ እንደደረሱ መግለጻቸውም አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)