ወደ አላማጣ ከተማ “ታጣቂ ኃይሎች እየገቡ ነው” ያሉ ነዋሪዎች፤ ትላንት እና ዛሬ የተቃውሞ ሰልፎች አካሄዱ 

በሙሉጌታ በላይ

ከተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወደ አላማጣ ከተማ እየተመለሱ ካሉ ተፈናቃዮች ጋር “ታጣቂ ኃይሎች አብረው እየገቡ ነው” በሚል በትላንትናው እና በዛሬው ዕለት በከተማይቱ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ። በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ ዝናቡ ደስታ፤ በከተማይቱ “ረብሻ ያስነሱት” የፕሪቶሪያው ስምምነት “ውድቅ እንዲሆን የሚፈልጉ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ናቸው” ሲሉ ወንጅለዋል። 

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የአላማጣ ከተማ፤ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል “የይገባኛል” ጥያቄ ከሚነሱባቸው አካባቢዎች አንዷ ነች። ከተማይቱ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል አስተዳደር ስር የቆየች ቢሆንም፤ ካለፈው ሚያዝያ ወር ወዲህ ግን በቦታው የነበረው አስተዳደር ፈርሶ አካባቢውን የመከላከያ ሰራዊት እንዲቆጣጠር ተደርጓል። 

ይህ እርምጃ የተወሰደው፤ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል “የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ ዘላቂነት ባለው መልክ እልባት ለመስጠት” የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በመጋቢት ወር አጋማሽ ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ነበር። በዚህ ስብሰባ መግባባት ላይ ከተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል “በአማራ ክልል የተመሰረቱ የአስተዳደር እና የጸጥታ መዋቅሮች እንዲፈርሱ” ማድረግ እና “ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው መመለስ” የሚለው ይገኝበታል።

በብሔራዊ ኮሚቴው የተፈናቃዮች መመለስ ስራን ለማከናወን እቅድ የያዘው “ሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ” በሚል ነበር። ሆኖም ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተፈናቃዮች፤ ወደ አላማጣ ከተማ መግባት የጀመሩት ከትላንት ረቡዕ ሐምሌ 10፤ 2016 ጀምሮ ነው። 

በትላንትናው ዕለት ከመኾኒ ከተማ ወደ አላማጣ ከተማ የገቡት ከ10,000 በላይ ተፈናቃዮች መሆናቸውን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሁለተኛ ዙር ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራም በዛሬው ዕለት መከናወኑንም ገልጸዋል። 

በዚህም መሰረት በማይጨው ከተማ ተጠልለው የቆዩ ከ1,000 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 11 ወደ አላማጣ ከተማ መግባታቸውን አስረድተዋል። ተፈናቃዮቹ በከተማይቱ ወደሚገኝ ስታዲየም እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እና ቤተሰቦቻቸውን እንዲቀላቀሉ መደረጉን ከንቲባው አመልክተዋል።

ፎቶ፦ የትግራይ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

ከእነዚህ ተፈናቃዮች ጋር “የትግራይ ክልል ታጣቂ ኃይሎች አብረው እንዲገቡ ተደርጓል” ያሉ የተወሰኑ የአላማጣ ነዋሪዎች ግን ይህንኑ ተቃውሟቸውን ለማሰማት ትላንት እና ዛሬ አደባባይ መውጣታቸውን የአይን እማኞች አስታውቀዋል። በቦታው የነበሩ አንድ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ የትላንትናው የተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደው “ወንጭፍ አደባባይ” በሚባለው ቦታ ላይ መሆኑን “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደ አላማጣ የገቡት በአውቶብስ፣ በሚኒባስ እና በሞተር ሳይክል ተጭነው እንደነበር የጠቀሱት እኚሁ ነዋሪ፤ እነርሱን ያጀቡ አራት አምቡላንስ መመልከታቸውን ተናግረዋል። አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች የትግራይ ክልል ባንዲራን ይዘው እንደነበርም ተናግረዋል።

“እንዲህ ሆነው ሲገቡ ወጣቱ አትገቡም አለ። ወዲያው መከላከያ መጥቶ ነገሩን እንዲረጋጋ አደረገ። እነሱም ወደ ስታዲዮም እንዲሄዱ ተደረገ” ሲሉ ትላንት የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል። በትላንቱ ሰልፍ “ህዝቡ በሰላም ነው ተቃውሞውን ያሰማው” ያሉት ነዋሪው፤ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የተቃውሞ ሰልፍ በወጣቶች መደረጉን ገልጸዋል። 

ዛሬ በተደረገው ሰልፍ የተሳተፉ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ፤ ተቃዋሚዎቹ ከትላንቱ አንጻር ቁጥራቸው “አነስ” ያሉ እንደሆኑ ጠቁመዋል። “የተፈናቃዮችን መምጣት ቀድመን እናውቃለን። ወደ ስታዲየም እንደሚወስዷቸውም [እናውቃለን]። የዛሬውን ሰልፍ ያደረግነው በዚሁ አካባቢ ነው” ሲሉ ተቃውሞው የተደረገበትን አካሄድ አስረድተዋል።

ወደ አላማጣ ከተማ እየተመለሱ ያሉት ተፈናቃዮች “በትክክል የከተማው ነዋሪዎች አይደሉም” የሚሉት ነዋሪው፤ ለተቃውሞው መቀስቀስ ምክንያት የሆነውን ጉዳይም ይኸው እንደሆነ ይናገራሉ። ትላንት እና ዛሬ ወደ አላማጣ ከተማ እንዲገቡ ከተደረጉት ተፈናቃዮች ውስጥ የተወሰኑት፤ “ጦርነቱ ከተቋጨ በኋላ ተመልሰው መጥተው አብረውን ሲኖሩ የነበሩ ናቸው” ሲሉም ይሟገታሉ። 

“በዚህ ሳምንት የመጀመሪያዎቹ ቀናት፤ የትግራይ ክልል መንግስት አላማጣ ከተማ ይኖሩ የነበሩ የክልሉን ተወላጆች የገንዘብ እና የተለያዩ ድጋፎችን ታገኛላችሁ በሚል ወደ መኾኒ ከተማ እንዲመለሱ አድርገዋቸዋል። ትላንት ወደ አላማጣ እንዲገቡ የተደረጉት ተፈናቃዮች እነዚሁ ወደ መኾኒ የተወሰዱት እና ታጣቂዎች ተቀላቅለው ነው” ሲሉም ነዋሪው ይከስሳሉ። 

“እኔ በአይኔ ያየሁት፤ አምስት እና ስድስት ሞተር ላይ [የተሳፈሩ] ክላሽ የያዙ ናቸው። ክላሹ ጥቁር ታጣፊ፣ መከላከያ የሚይዘው ዓይነት ነው። ‘ተፈናቃይ ነኝ’ እያልክ እንዴት መሳሪያ ትይዛለህ?”

– በተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉ አንድ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ

ከተፈናቃዮቹ ጋር “መሳሪያ የታጠቁ ሰዎችን” መመልከታቸውንም ለዚህ በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። “እኔ በአይኔ ያየሁት፤ አምስት እና ስድስት ሞተር ላይ [የተሳፈሩ] ክላሽ የያዙ ናቸው። ክላሹ ጥቁር ታጣፊ፣ መከላከያ የሚይዘው ዓይነት ነው። ‘ተፈናቃይ ነኝ’ እያልክ እንዴት መሳሪያ ትይዛለህ?” ሲሉም ነዋሪው ይጠይቃሉ። 

እርሳቸውን ጨምሮ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች፤ “ትክክለኛ” ሲሉ የሚገልጿቸው ተፈናቃዮች ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን በመጥቀስ ይከራከራሉ። በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ከአላማጣ ከተማ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያቸው የመለሰው፤ በወቅቱ ከተማይቱን ያስተዳድር የነበረው በአማራ ክልል ስር የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር እንደነበርም ይጠቅሳሉ።  

ሶስቱም ነዋሪዎች አሁን እየተደረገ ያለው “ተፈናቃዮችን ሳይሆን ታጣቂዎችን ወደ ከተማይቱ የማስገባት ስራ ነው” የሚል እምነት አላቸው። ይህን የነዋሪዎችን አስተያየት፤ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ በመሆን እያገለገሉ ያሉት አቶ ዝናቡ “ፍጹም ስህተት ነው” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

“የገባን ተፈናቃይ እንደገና ማስገባት፤ የፖለቲካ ነው ወይስ የኢኮኖሚ ትርፍ የምታገኘው? ምንም በዚህ የሚገኝ ጥቅም የለም”

– አቶ ዝናቡ ደስታ፤ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ

“እንዲህ ማድረግ ምንድነው ጠቀሜታው? የገባን ተፈናቃይ እንደገና ማስገባት፤ የፖለቲካ ነው ወይስ የኢኮኖሚ ትርፍ የምታገኘው? ምንም በዚህ የሚገኝ ጥቅም የለም” ሲሉ አቶ ዝናቡ የነዋሪዎቹን አስተያየት አጣጥለዋል። በአላማጣ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ፤ ተፈናቃዮች ገብተው ከጨረሱ በኋላ “ወጣቶች በመበሻሸቅ ያደረጉት ነው” ሲሉም ተቃውሞውን አቃልለውታል። 

“ትላንት ሲረብሽ የነበረው፤ አመጽ ለማስነሳት እና እኛ እርምጃ እንድንወስድ ነው። በዚያ አድርጎ ነገሮች እንዲባባሱ እና ከመጋጨት አልፎ ወደ ጦርነት እንዲገባ ነው” ሲሉም አቶ ዝናቡ ከተቃውሞው ጀርባ አለ ያሉትን አላማ አስረድተዋል። “ረብሻውን” ያስነሱት፤ “የፕሪቶሪያው ስምምነት ውድቅ እንዲሆን የሚፈልጉ አካላት ናቸው” ሲሉም የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ወንጅለዋል። 

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት፤ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በፌደራል መንግስት መካከል የተፈረመው በጥቅምት 2015 ዓ.ም ነበር። ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ ከደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል “የጸጥታ ሁኔታው ሲፈቅድ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ” የሚለው ይገኝበታል። ትላንት እና ዛሬ ወደ አላማጣ ከተማ ከተመለሱት በተጨማሪ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ በመቐለ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ 2,000 የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ መታቀዱን የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)