በቤርሳቤህ ገብረ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፒያሳ በኮሪደር ልማት ያጸዳቸውን አካባቢዎች ጨምሮ በስምንት ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ መሬቶች ያወጣው ሶስተኛ ዙር የሊዝ ጨረታ፤ ለተጨማሪ 10 ቀናት ተራዘመ። ከዛሬ ሰኞ ሐምሌ 15፤ 2016 ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ሊካሄድ የነበረው ጨረታ የተራዘመው፤ “በቂ ተጫራቾች ባለመገኘታቸው ነው” ተብሏል።
የከተማይቱ አስተዳደር የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ለሶስተኛው ዙር ጨረታ ያቀረባቸው መሬቶች ብዛት 228 ነው። ከእነዚህ መሬቶች ውስጥ የተወሰኑት ከዚህ ቀደም የነበራቸው የሊዝ ውላቸው ተቋርጦ ወደ መሬት ባንክ የገቡ መሆናቸው ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ በማድረግ ላይ በሚገኘው “የመንገድ ኮሪደር ልማት” ሳቢያ እንዲጸዱ በተደረጉ አካባቢዎች የሚገኙ መሬቶችም እንዲሁ በሶስተኛው ዙር ጨረታ እንዲካተቱ ተደርገዋል። እነዚህ መሬቶች በአብዛኛው የሚገኙት በአራዳ ክፍለ ከተማ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አቅራቢያ ባሉ የፒያሳ አካባቢዎች ነው።
ሌሎቹ መሬቶች የሚገኙት በየካ፣ በንፋስ ስልክ፣ በኮልፌ ቀራንዮ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በአዲስ ከተማ፣ ልደታ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች በጨረታ ሰነድ ዝርዝሩ ላይ ተመላክቷል። የሶስተኛውን ዙር የሊዝ ጨረታ ሰነድ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ለሽያጭ ያቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፤ የተጫራቾችን የመወዳደሪያ ዋጋ ከዛሬ ጀምሮ ይፋ ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ይዞ ነበር።
በዛሬው ዕለት በቦሌ ክፍለ ከተማ አዳራሽ ሊከፈት የነበረው ጨረታ፤ “በቂ ተጫራቾች ባለመገኘታቸው” ለተጨማሪ 10 ቀናት መራዘሙን በቢሮው የለማ መሬት ማስተላለፍ እና ሊዝ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ጫሊ አብርሃም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቢሮው ለጨረታ የወጡ መሬቶች “በቂ ተጫራቾች አግኝተዋል” ብሎ ካላሰበ፤ ጨረታውን የማራዘም መብት እንዳለው አቶ ጫሊ አስረድተዋል።
የጨረታው መውጣት በበቂ ተጫራቾች አልተሰማም ተብሎ ከታሰበ አንዲሁም ከጨረታ ሰነድ ሽያጭ የተገኘው ገቢ ለጨረታው የወጣውን ገቢ መሸፈን ካልቻለ፤ በተመሳሳይ መልኩ የሊዝ ጨረታዎች እንዲራዘሙ ምክንያት ሊሆን እንደሚችሉም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። በ2004 ዓ.ም. የጸደቀው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ፤ መሬት በምደባ እና በጨረታ እንደሚተላለፍ ይደነግጋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአራት ዓመታት አቋርጦ የቆየውን የመሬት ሊዝ ጨረታ መልሶ የጀመረው በግንቦት 2015 ዓ.ም. ነበር። የከተማይቱ አስተዳደር ባለፈው ግንቦት ወር ባካሄደው ሁለተኛ ዙር ጨረታ፤ ከ240 በላይ ቦታዎች ለሊዝ ሽያጭ ቀርበዋል።
የከተማይቱ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፤ በሁለተኛው ዙር ጨረታ 4,201 የጨረታ ሰነዶች የሸጠ ሲሆን ከመሬት ሊዝ ሽያጭም 3.5 ቢሊየን ብር ያህል ገቢ ማግኘቱን አቶ ጫሊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የእዚህ ዙር ጨረታ አሸናፊዎች “ውል እየገቡ እና ስራም እየጀመሩ መሆናቸውን” ዳይሬክተሩ አክለዋል።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ አሁን ለጨረታ ከቀረቡ ቦታዎች ውስጥ 60 የሚሆኑት በሁለተኛው ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ ውል ያልተፈጸመባቸው ናቸው። በግንቦቱ ጨረታ ትልቁ ዋጋ ተሰጥቶ የነበረው መሬት በካሬ 410,000 ብር የተመዘገበበት ነው። በሁለተኛው ዙር ጨረታ፤ በካሬ 20,100 ብር ዋጋ የቀረበበት መሬት ትንሹ መጠን ሆኖ ተመዝግቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 ዓ.ም. በጀት አመት ከመሬት ሊዝ ሽያጭ ለማግኘት ያቀደው ገቢ 40 ቢሊየን ብር ነው። አስተዳደሩ የመሬት ሊዝ ጨረታን መልሶ በጀመረበት በግንቦት 2015 ከተመሳሳይ የገቢ ምንጭ ለማግኘተ አቅዶ የነበረው 12.2 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)