በሙሉጌታ በላይ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት፤ የሁልባረግ ዳሎቻ ምርጫ ክልል ተወካይ የሆኑት የአቶ መዚድ ራህመቶን ያለመከሰስ መብት አነሳ። የምክር ቤቱ አባል “ተደራራቢ ወንጀሎችን በመፈጸም” የተጠረጠሩ በመሆናቸው የህግ ከለላቸው እንደተነሳ ተገልጿል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 17፤ 2016 ማካሄድ በጀመረው መደበኛ ጉባኤ፤ ለውይይት ከያዛቸው 10 አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ የአቶ መዚድን ያለመከሰስ መብት ማንሳት ነበር። የአቶ መዚድን ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ጥያቄ ያቀረበው፤ የክልሉ ፍትህ ቢሮ እንደሆነ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ገልጸዋል።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ከአንድ ሳምንት በፊት ሐምሌ 11፤ 2016 በጻፈው ደብዳቤ፤ የምክር ቤት አባሉ “የተጠረጠሩበት ወንጀል ከባድ” የሚባል እንደሆነ መጥቀሱን በዛሬው ጉባኤ ላይ ተነግሯል። ተጠርጣሪውን “ለመክሰስ እና ለመያዝ እንዲቻል” የህግ ከለላቸው እንዲነሳ በቀረበው ጥያቄ መሰረት፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የሕግ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን ሲመረምር መቆየቱም ተጠቅሷል።
ቋሚ ኮሚቴው የምክር ቤት አባሉ በተጠረጠሩበት ወንጀል “ለጥርጣሬ የሚያበቃ ግንኙነት ስለመኖሩ ለማጣራት”፤ በክልሉ ፍትህ ቢሮ የተደራጀውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን የያዘ ባለ 112 ገጽ መዝገብ መመልከቱን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ መሰረት ወልደ ሰንበት ለክልሉ ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። በዚህ መሰረት “ወንጀሉ ስለመፈጸሙ ባደረገው ማጣራት ለጥርጣሬ የሚያበቃ መሆኑን ማረጋገጥ” እንደቻለ አብራርተዋል።
አቶ መዚድ ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች መካከል “በስልጣን አላግባብ መገልገል” አንዱ እንደሆነ በዛሬው ጉባኤ ላይ ተገልጿል። የምክር ቤት አባሉ “የመንግስት ስራ በማያመች አኳኋን መምራት” እና “ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራት” በሚሉ ተደራራቢ ወንጀሎች እንደተጠረጠሩም ተነግሯል። በዚህ ምክንያት ከሁልባረግ ዋና አስተዳዳሪነት ከስድስት ወር በፊት እንዲነሱ መደረጋቸውም በተጨማሪነት ተጠቅሷል።
ተጠርጣሪው የሁልባረግ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት በ2014 ዓ.ም ነበር። በሁልባረግ ወረዳ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የሰሩት አቶ መዚድ፤ በወረዳው በሚገኙ የተለያዩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም በመምህርነት አገልግለዋል። የሁልባረግ ወረዳን እንዲያስተዳድሩ ከመመደባቸው አስቀድሞ የስልጤ ዞን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ በመሆን ለአንድ ዓመት አገልግለዋል።
የሁልባረግ ዳሎቻ ምርጫ ክልልን በመወከል የቀድሞውን የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ምክር ቤትን በ2014 ዓ.ም. የተቀላቀሉት አቶ መዚድ፤ ነባሩ ክልል ፈርሶ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በነሐሴ 2015 ሲመሰረትም የአዲሱ ክልል ምክር ቤት አባል ሆነዋል። የአቶ መዚድ ያለመከሰስ መብት መነሳትን በተመለከተ በዛሬው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ፤ በሶስት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)