የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ በሚያደርጋቸው በረራዎች ላይ እገዳ እንደተጣለበት አረጋገጠ 

በቤርሳቤህ ገብረ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት ወር በኋላ ወደ ኤርትራ በሚያደርጋቸው በረራዎች ላይ እገዳ እንደተጣለበት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋገጡ። አየር መንገዱ የእገዳ ውሳኔውን የሰማው፤ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ቁጥር ለመጨመር ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እየተነገጋረ ባለበት ወቅት መሆኑን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ተደርጎ የነበረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተቋርጦ የነበረው የአየር በረራ ግንኙነት እንደገና መልሶ የጀመረው የዛሬ ስድስት ዓመት ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ የመጀመሪያውን የንግድ በረራ ወደ ኤርትራ መዲና አስመራ ያደረገው በሐምሌ 11፤ 2010 ዓ.ም ነበር።

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከሰኞ እና ማክሰኞ በስተቀር በሳምንት ለአምስት ቀናት ወደ አስመራ ከተማ  በረራዎች እያደረገ ቢገኝም፤ የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በዛሬው ዕለት ባወጣው ማስታወቂያ ግን በረራዎቹ ከመጪው መስከረም 20፤ 2017 በኋላ እንደሚቋረጡ አስታውቋል። 

ይህ ማስታወቂያ ዛሬ ሐምሌ 17፤ 2024 በታተመው መንግስታዊው “ሓዳስ ኤርትራ” ጋዜጣ ላይ ታትሞ መውጣቱን “ቢቢሲ አማርኛ” የዜና አውታር ዘግቧል። በማህበራዊ የትስስር ገጾች የተጋራው እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተሰራጨው የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ማስታወቂያ፤ መስሪያ ቤቱ ይህን እርምጃ ለመውሰድ “የተገደደበትን” ምክንያት ዘርዝሯል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ “በተደራጀ እና ዘዴዎችን” በተከተለ መንገድ “እየፈጸማቸው ነው” በሚል በባለስልጣኑ ከተወነጀለባቸው ድርጊቶች መካከል፤ “የመንገደኞች ሻንጣ ስርቆት፣ ዘረፋ እና ጉዳት” ይገኝበታል። አየር መንገዱ በበረራዎች ላይ “የተራዘሙ መዘግየቶች” መፍጠሩ እና “አግባብ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉም” በባለስልጣኑ ከተጠቀሱ “ጥፋቶች” መካከል ይጠቀሳሉ።  

ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ “በኢኮኖሚ ክላስ” ለመጓዝ፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያስከፍለው  ዝቅተኛ የደርሶ መልስ ትኬት ዋጋ 19 ሺህ ብር ገደማ ነው። አየር መንገዱ ከሁለት ሳምንት በፊት የበረራ ዋጋውን ወደ 85 ሺህ ብር አድርሶት እንደነበር የመስሪያ ቤቱ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ ለመጓዝ ያቀዱ መንገደኞች፤ ከመስከረም 20 በኋላ ያሉ በረራዎቻቸውን እንዲያስተካክሉ አሊያም ሌሎች አማራጭ መንገዶች እንዲመለከቱ የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በዛሬው ማስታወቂያው አሳስቧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትኬት የሚሸጥበት ይፋዊ ድረ ገጽ ግን ከቀነ ገደቡ በኋላ ያሉትን ቀናት አሁንም ለመንገደኞች ክፍት አድርጓቸዋል። 

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እግዱ መጣሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም፤ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል። የአየር መንገዱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሃና አጥናፉ፤ አስመራ ለሚገኘው ኤርያ ማናጀር ባለፈው እሁድ ደብዳቤ እንደደረሰው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ኃላፊዋ “ባለ አንድ መስመር” ሲሉ በገለጹት ደብዳቤ ላይ የበረራ እገዳው ቢጠቀስም፤ ነገር ግን ምክንያቱ አለመዘርዘሩን አስረድተዋል። አየር መንገዱ በሳምንት ውስጥ የሚያደርገውን በረራ ከ10 ወደ 15 ማሳደግ እንደሚችል ከሁለት ሳምንት በፊት ተገልጾለት እንደነበር የጠቀሱት ሃና፤ “እርሱ ላይ አየተዘጋጀን እና እየተነጋገርን ሳለ የደረሰን ደብዳቤ አስደንጋጭ ነው” ብለዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድን በተመለከተ በዛሬው ዕለት በጋዜጣ የወጣውን ማስታወቂያ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተሰራጨውን ማየታቸውን ነገር ግን ምንም ለእነርሱ በቀጥታ አንዳልደረሳቸው ኃላፊዋ ምላሽ ሰጥተዋል። ጉዳዩን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋናው መስሪያ ቤት እና በአስመራ ኤሪያ ማናጀር በኩል ግንኙነት ለማድረግ እየሞከሩ መሆኑንም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)