በሙሉጌታ በላይ
ላለፉት ዘጠኝ አመታት በስራ ላይ የቆየውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላትን የሚተኩ ተመራጮች፤ በነገው ዕለት የአዲሱን ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ሊያካሄዱ ነው። ነገ ማክሰኞ ሐምሌ 23፤ 2016 በሚደረገው በዚህ ጉባኤ ላይ “የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንደሚሰይም” የተሰናባቹ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት 99 መቀመጫዎች አሉት። በ2007 ዓ.ም በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ የተመረጡ የምክር ቤቱ አባላት እስከ ትላንት ድረስ በስራ ላይ ቆይተዋል። እነዚህ የምክር ቤት አባላት ከአንድ የምርጫ ዘመን ጊዜ በላይ በስራ ላይ የቆዩት፤ በ2013 ዓ.ም በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉ ነው።
በ2013 እና 2016 ዓ.ም በተደረጉ ምርጫዎች፤ 88ቱን የምክር ቤት መቀመጫዎች ያሸነፈው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ነው። ባለፈው ሰኔ ወር በተካሄደው “ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ”፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) እና የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ተወካዮቻቸውን ለክልሉ ምክር ቤት ማስመረጥ ችለዋል።
ጉህዴን ስምንት የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫዎች ሲያሸንፍ፤ ቦዴፓ በበኩሉ በሁለት ተመራጮቹ በምክር ቤቱ ይወከላል። የሰኔውን ምርጫውን ያሸነፉት እነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች፤ በነገው የክልሉ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደደረሳቸው “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
በአሶሳ ከተማ በሚካሄደው በዚሁ መስራች ጉባኤ፤ ባለፈው ሰኔ በተካሄደው “ቀሪ እና ድጋሚ” ምርጫ የተመረጡ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ ዶ/ር ተመስገን አስታውቀዋል። በነገው ጉባኤ፤ ምክር ቤቱን የሚመሩ አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈጉባኤ እንደሚመረጡም አክለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ አፈ ጉባኤ የሚመረጠው “በምክር ቤቱ የስራ ዘመን መጀመሪያ” ላይ መሆኑን ይገልጻል። የምርጫ ሂደቱም “በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት የመድረክ መሪነት” እንደሚከናወን በደንቡ ላይ ሰፍሯል።

ለግማሽ ቀን ይቆያል በተባለው በነገው ጉባኤ ከተያዙት አጀንዳዎች ውስጥ፤ “የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር መሰየም” የሚለው ይገኝበታል። በአሁኑ ወቅት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ አሻድሊ ሀሰን ናቸው። አቶ አሻድሊ በ2008 ዓ.ም. ወደ ስልጣን የመጡት፤ ከእርሳቸው በፊት ለሰባት ዓመታት ክልሉን ሲያስተዳድሩ የቆዩት አቶ አህመድ ናስር “በድንገት ሕይወታቸው ማለፉን” ተከትሎ ነው።
በወቅቱ የክልሉ ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ፤ በጊዜው የክልሉ ገዢ ፓርቲ በነበረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጉህዴፓ) አቅራቢነት አቶ አሻድሊ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል። በነገው የክልሉ ምክር ቤት መስራች ጉባኤ፤ አቶ አሻድሊ በርዕሰ መስተዳድርነት ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ዶ/ር ተመስገን ግምታቸውን አጋርተዋል።
ተሿሚው ርዕሰ መስተዳድር፤ የክልሉን መንግስት ካቢኔ አባላት ለምክር ቤቱ አቅርበው እንደሚያጸድቁ ይጠበቃል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ሹመትም በተመሳሳይ መልኩ ለአባላት ከቀረበ በኋላ እንደሚጸድቅ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)