በናሆም አየለ
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ባለፈው የ2016 በጀት ዓመት ባከናወናቸው የመንገድ ግንባታ ሳቢያ ለተነሱ መሰረተ ልማቶች እና የመኖሪያ ቤቶች 1.8 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙን ገለጸ። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዘንድሮው በጀት ዓመት በሚገነባቸው መንገዶች እና ከሁለተኛው ዙር የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ 546 የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶች እንደሚነሱ አስታውቋል።
መስሪያ ቤቱ ይህንን ያስታወቀው፤ ያለፈውን አመት የስራ አፈጻጸሙን እና የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት እቅድ አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 9፤ 2017 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ነው። የአዲስ አበባ ከተማን የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲገነባ እና እንዲጠግን በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጠው መስሪያ ቤቱ፤ በ2016 በጀት ዓመት 1,140 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ እና ጥገና ማከናወኑን በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል።
በመንገድ ግንባታ እና ጥገናው ሳቢያ 682 ቤቶች እንዲነሱ መደረጋቸውን የገለጸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ከ1,200 በላይ በሆኑ የመብራት እና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይም ተመሳሳይ እርምጃ መወሰዱን አመልክቷል። ቤቶቹ እና መሰረተ ልማቶቹ እንዲነሱ የተደረጉት፤ መንገዶች በሚገነቡበት “ወሰን ውስጥ የሚገኙ” በመሆናው ምክንያት መሆኑን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በመንገድ ስራው ተነሺ ለሆኑ ነዋሪዎች እና መሰረተ ልማቱን ለገነቡ ተቋማት ተገቢውን ካሳ መከፈሉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት ለካሳ የከፈለው የገንዘብ መጠን 1.1 ቢሊዮን ብር መሆኑ በዛሬው ውይይት ላይ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ተግባራዊ ማድረግ በጀመረው የኮሪደር ልማት ምክንያት ለተከናወኑ የመንገድ ግንባታዎች፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተጨማሪነት 795 ሚሊዮን ብር ካሳ መክፈሉም በውይይቱ ተጠቅሷል።
ይህ የካሳ ክፍያ የተፈጸመው “ለንግድ እና ለመኖሪያ ቤቶች ብቻ” መሆኑን የመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ በይፋ በተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እና መስሪያ ቤቱ በዚህ ዓመት ሊገነባቸው ካቀዳቸው መንገዶች ጋር በተያያዘ፤ 546 የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ከ1,800 በላይ የመብራት እና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች እንደሚነሱ በዛሬው ውይይት ላይ ይፋ ተደርጓል።
በአዲስ አበባ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ይከናወንባቸዋል ከተባሉት አካባቢዎች ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቅራቢያ የሚገኙት የአዋሬ እና የካዛንቺስ ስፍራዎች ይገኙበታል። ከመስቀል አደባባይ እስከ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ከሜክሲኮ አደባባይ አድዋ ድልድይ፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ፣ ከጣሊያን ኤምባሲ ጀርባ አንስቶ ከግንፍሌ ወንዝ ድረስ ያሉ አካባቢዎችም የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አካል እንደሚሆኑ ተነግሯል።
ከአፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር እስከ ጎሮ እንዲሁም ከአራት ኪሎ በእንጦጦ አድርጎ እስከ ጉለሌ የእጽዋት ማዕከል ባለው መንገድ አካባቢ ያሉ ስፍራዎችም ልማቱ ይከናወንባቸዋል የተባሉ ቦትዎች ናቸው። ነው። ከእንጦጦ በፒያሳ አድርጎ እስከ ፒኮክ መናፈሻ ያለውን የወንዝ ዳር ፕሮጀክትም፤ የሁለተኛው የኮሪደር ልማት አካል ሆኑ እንዲለማ እቅድ ተይዞለታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)