በቤርሳቤህ ገብረ
በክልሎች ስር ያሉ የትምህርት ተቋማት የሚመዘግቧቸውን እና የሚያደራጇቸውን መረጃዎች፤ ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲልኩ የሚያስገድድ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ። ለሚኒስቴሩ “ያልተሟላ መረጃ መላክም” ሆነ “ያልተፈቀደ መረጃን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት” በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ረቂቅ መመሪያው ይደነግጋል።
“የትምህርት መረጃ አስተዳደር ስርዓት መመሪያ” በሚል የተዘጋጀው ይህ መመሪያ፤ በአምስት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን 25 አንቀጾችን በውስጡ ይዟል። “የመረጃ ደህንነት፣ አስተዳደር፣ አፈጻጸም እና ቅጣትን” ያካተተው ይህ መመሪያ፤ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 8፤ 2017 በህዝብ አስተያየት መድረክ ላይ ውይይት ተደርጎበታል።
ትምህርት ሚኒስቴር የህግ ማዕቀፉን ያዘጋጀው፤ በትምህርቱ ዘርፍ ሁለንተናዊ እድገትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ “የትምህርት መረጃ” ያለውን “የማይተካ ሚና” ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው ረቂቅ መመሪያ ላይ ተጠቅሷል። የመመሪያው መዘጋጀት፤ ሚኒስቴሩ በትምህርት መረጃ አሰባሰብ፣ አተናተን እና አሰረጫጨት ረገድ በህግ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለው መሆኑም በረቂቅ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

የትምህርት መረጃ ለባለድርሻ አካላት በጊዜ እና በጥራት ተደራሽ ባለመሆኑ፤ “በትምህርት ስርዓቱ ሊወሰዱ በሚገባቸው የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ” ረቂቅ መመሪያው ለመዘጋጀቱ በተጨማሪ ምክንያትነት ተነስቷል። በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መረጃ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰብስቤ ለማም፤ ባለፈው ረቡዕ በተካሄደው የህዝብ አስተያየት ማሰባሰቢያ ውይይት ላይ ይህንኑ አስተጋብተዋል።
“ባለፉት ጊዜያት የነበረውን አካሄድ ስንመለከት፤ የመረጃ መውጣት እና መውረድ አለ። መረጃዎች በምንፈልጋቸው ጊዜ እና ወቅት ደርሰው፤ ለምንፈልጋቸው ግብአቶች እየዋሉ አልነበረም። ተአማኒነት የሌላቸው እና ወጥ ያልሆኑ መረጃዎች እንዳሉ የሚያሳይ ጥናት አለ። ይሄ ሁሉ ሆኖ ደግሞ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር የምንጠይቅበት ስርዓት አልነበረም” ሲሉ አቶ ሰብስቤ አብራርተዋል።
ይህን ችግር የመቅረፍ አላማ ያለው አዲሱ መመሪያ፤ የትምህርት መረጃ አስተዳደር ስርዓቱን “በአግባቡ ለመምራት” እና “ወጥ የሆነ የመረጃ ስርዓትን ለማረጋገጥ የሚያስችል” መሆኑ በረቂቅ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። የመረጃ አስተዳደር ስርዓትን መዘርጋት፤ በትምህርት ዘርፉ ለሚደረግ እቅድ፣ ዝግጅት፣ ክትትል እና ግምገማ የሚረዳ መሆኑን ረቂቅ መመሪያው ይገልጻል።

የመረጃ አስተዳደር ስርዓቱ ፖሊሲ ለማውጣት እና ለመተንተን እንዲሁም ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ከመጥቀሙ ባሻገር፤ ለተለያዩ ጥናቶች ግብዓት የሚሆን የተሟላ መረጃ የሚደራጅበት ሂደት መሆኑም በረቂቅ መመሪያው ተመላክቷል። ስርዓቱ በመረጃ ፍሰቱ ውስጥ የሚሳተፈውን “የሰው ኃይል፣ ቴክኖሎጂን፣ ሞዴሎችን፣ ዘዴዎችን፣ ሂደቶችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን እና ማብራሪያዎችን” እንደሚያካትትም ረቂቅ ሰነዱ አስገንዝቧል።
በዚህ መልኩ በሚዘረጋው ስርዓት አማካኝነት “የሚጠናቀሩ” እና “የሚተነተኑ” የትምህርት መረጃዎች የትኞቹ እንደሆኑ ረቂቅ መመሪያው ዘርዝሯል። የአንድ ትምህርት ቤት አጠቃላይ ሁኔታ፣ የተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የርዕሰ መምህራን፣ የምክትል ርዕሰ መምህራን፣ የሱፐርቫይዘር እና ሌሎች የአስተዳደር ሰራተኞች መረጃ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ ይገኙበታል።
የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቅበላ፣ የተመራቂ ተማሪዎች እና የስራ ስምሪታቸው ሁኔታ እንዲሁም በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ በመረጃነት እንዲሰበሰቡ ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል ተመድበዋል። የትምህርት ቤቶች እና ተቋማት ህንጻዎች፤ የመሰረተ ልማት፣ የመጻህፍት እና ሌሎች ቁሳቁሶች፣ የውሃ አቅርቦት፣ ስነ ጤና እና ንጽህና አጠባበቅ መረጃዎችም እንዲሁ በትምህርት መረጃነት እንደሚሰበሰቡ እና እንደሚጠናቀሩ በረቂቅ መመሪያው ላይ ሰፍሯል።

ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ አጠቃላይ የትምህርት ተቋማትን የሚመለከተው ይህ ረቂቅ መመሪያ፤ የፋይናንስ ገቢ እና ወጪን የሚመለከቱ መረጃዎች ጭምር እንዲሰበሰቡ ያዝዛል። በዚህ መልኩ የሚሰበሰቡ መረጃዎች፤ በትምህርት ተቋማት፤ በአስተዳደር እርከኖች እና በመምህራን ኮሌጆች በሚቋቋሙ ማዕከላት እንዲደራጁ እና እንዲረጋገጡ ያዝዛል።
በእነዚህ ማዕከላት የተጠናቀሩ መረጃዎችን የሚቀበሉ የክልል የትምህርት መረጃ አስተዳደር ስርዓት ማዕከላት፤ መረጃዎቹን ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲልኩ መመሪያው ያስገድዳል። እነዚህ የክልል ማዕከላት፤ የትምህርት ዘመኑን መረጃ ለሚኒስቴሩ የመላክ ግዴታ የተጣለባቸው በየዓመቱ ጥር ወር ውስጥ ነው።
የክልል ማዕከላቱ “ዓመታዊ የትምህርት ስታቲስቲካል አብስትራክት” በድረ ገጽ ወይም በወረቀት በማዘጋጀት ለባለድርሻ አካላት እንዲያዘጋጁ የሚጠበቅባቸው ደግሞ በእያንዳንዱ የትምህርት ዘመን በግንቦት ወር ውስጥ ነው። ተመሳሳዩ መረጃ በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች የሚቀርበው በየዓመቱ በሰኔ ወር ውስጥ እንደሆነ በረቂቅ መመሪያው ተደንግጓል።

ረቂቅ መመሪያው የትምህርት መረጃዎች ለተጠቃሚዎች ወይም ለባለድርሻ አካላት የሚቀርቡበትን የጊዜ ሰሌዳ ቢዘረዝርም፤ መረጃ ማጋራት የማይቻልበትን ሁኔታ አብሮ አካትቷል። “ማንኛውም መረጃ በሚኒስቴሩ የትምህርት መረጃ አስተዳደር ማዕከል ወይም በአስተዳደር እርከን ባሉ እና በተፈቀደላቸው የትምህርት መረጃ አስተዳደር ስርዓት ማዕከላት ሳይረጋገጥ ወይም ይፋ ሳይደረግ ለተጠቃሚ ማጋራት አይቻልም” ሲል ረቂቅ መመሪያ ይከለክላል።
በመመሪያው “ያልተፈቀደን መረጃ ለሌላ ሶስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠትን” ጨምሮ ሌሎች በህግ ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ጉዳዮች፤ ለውይይት በቀረበው የህግ ማዕቀፍ ላይ ሰፍረዋል። በመመሪያው በተቀመጠው አግባብ ወይም የጊዜ ሰሌዳ መረጃ አለመላክ በህግ እንደሚያስጠይቅ ረቂቅ መመሪያው ደንግጓል። “አግባብነት የሌለው”፣ “ያልተሟላ”፣ “በተለያየ ደረጃ ጥራቱን ያልጠበቀ” የትምህርት መረጃን መላክም ተመሳሳይ ተጠያቂነት ያስከትላል።
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መረጃ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰብስቤ ለማ ቅጣትን በተመለከተ በመመሪያው ላይ የተካተተው አንቀጽ፤ አሁን በተግባር ላይ ያሉ ህጎችን እና ሌሎችን ነገሮች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል። ረቂቅ መመሪያው ለፍትህ ሚኒስቴር ከተላከ በኋላ “ለውጦች” ሊደረጉበት ሊኖሩት እንደሚችሉም ጥቆማ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)