በቤርሳቤህ ገብረ
በኢትዮጵያ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የወንጀል ድርጊቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ተናገሩ። ኢትዮጵያ የገጠሟት ግጭቶች ካስከተሏቸው ዳፋዎች ለማገገም “አመታት ሊወስድባት” እንደሚችልም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ ይህን የተናገሩት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በኢትዮጵያ ምክክር እና ሰላምን ለመደገፍ ላለፉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን ፕሮጀክቶች መጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ ባሰሙት ንግግር ነው። በአዲስ አበባው ሸራተን ሆቴል በተካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ፤ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደረገባቸው ዓመታት ያጋጠሙ ስኬቶች እና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይቶች ተካሄደዋል።
የመርሃ ግብሩ ቁልፍ ተናጋሪ የነበሩት የአሜሪካው አምባሳደር፤ በኢትዮጵያ ከአስር ዓመት በፊት ለተከታታይ ዓመታት ይመዘገብ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት በባለፈው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት መቀነሱን አስረድተዋል። ለዚህ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በሀገሪቱ ያለው ግጭት “ዋነኛ ሚና” መጫወቱንም አስገንዝበዋል።
ግጭት በህጻናቶች ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ “ከፍተኛ” መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ለዚህም በማሳያነት በአማራ ክልል ከትምህርት የተስተጓጉሎ ተማሪዎችን አንስተዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በክልሉ በግጭት ሳቢያ 4.1 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ማስታወቁን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።
ይኸው ሪፖርት በአማራ ክልል 4,178 ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ መግለጹን ማሲንጋ አስታውሰዋል። በኢትዮጵያ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የወንጀል ድርጊቶች እየጨመሩ መምጣታችውን ሁሉም የሚታዘበው ጉዳይ መሆኑንም የአሜሪካው አምባሳደር አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ግጭት ችግሮችን በመፍጠር፣ በፍጥነት በማስፋፋት እና በስፋት እንዲሰራጩ በማድረግ፤ በሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ላይ በመጥፎ መንገዶች ተጽእኖ የሚያሳድር ነው” ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ኢትዮጵያ የገጠሟት ግጭቶች ካስከተሏቸው ዳፋዎች ለማገገም “አመታት ሊወስድባት” እንደሚችልም አመልክተዋል።ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሰፍን “በጋራ መስራት” የሚያስፈልገውም በዚህ ምክንያት መሆኑን አክለዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ በዛሬው ንግግራቸው የሰላም እና የውይይትን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ አንስተዋል። ግጭቶችን ለማስቆም፣ የጋራ መግባባትን እና መፍትሔ ለማበጀት እና “ብቸኛው መንገድ” ውይይት ማድረግ መሆኑንም አበክረው ገልጸዋል። የአሜሪካው አምባሳደር ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር ላይም ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀው ነበር። አምባሳደሩ በወቅቱ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች “ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ ማቆም” እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)