በቤርሳቤህ ገብረ
የሶስት አመት የስራ ዘመኑን እያገባደደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን በመጪው ማክሰኞ በሚካሄድ አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ሊያቀርብ ነው። በዚሁ ስብሰባ ላይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “የስራ ዘመን ይራዘማል” ተብሎ እንደሚጠበቅ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በታህሳስ 2014 ዓ.ም የጸደቀው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ሶስት ዓመት እንደሆነ ይደነግጋል። የኮሚሽኑ የስራ ዘመን የሚቆጠረው፤ በአዋጁ መሰረት የሚመረጡ ኮሚሽነሮች በፓርላማ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ በድንጋጌው ላይ ሰፍሯል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዕጩነት የቀረቡ 11 ኮሚሽነሮችን ሹመት ያጸደቀው የካቲት 14፤ 2014 ዓ.ም. ነው። ፓርላማው ለአንድ ወር እረፍት የተበተኑ አባላቱን ለመጪው ማክሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው፤ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ድፍን ሶስት ዓመት ከሚሞላበት ዕለት ሁለት ቀናት አስቀድሞ ነው።

የተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ለአባላቱ ባሰራጨው የስብሰባ ጥሪ፤ ለኮሚሽኑ ጥያቄ ማቅረብ የሚፈልጉ አባላት እስከ ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 8፤ 2017 ድረስ እንዲመዘገቡ አሳስቦ ነበር። ተጠሪነቱ ለተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፤ አስቸኳይ ስብሰባው ከመጠራቱ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ፤ ለፓርላማው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት አቅርቦ ነበር።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ያቀረቡት ይህ ሪፖርት፤ የተቋሙን የሶስት ዓመት የስትራቴጂ ዕቅድ የስራ አፈጻጸም የሸፈነ ነው። ዋና ኮሚሽነሩ ባለፈው ህዳር ወር መጀመሪያ በፓርላማ በመገኘት የኮሚሽኑን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በተመሳሳይ መልኩ ባቀረቡበት ወቅት፤ የተቋሙ የስራ ዘመን መገባደድን የተመለከተ ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር።
በዚሁ ስብሰባ ላይ ጥያቄ ለመጠየቅ እድል ከተሰጣቸው 10 የፓርላማ አባላት መካከል አምስቱ፤ ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን የስራ ዘመን ለማጠናቀቅ በቀሩት ሶስት ወራት ውስጥ እንዴት ስራዎቹን እንደሚጨርስ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። እነዚሁ የፓርላማ አባላት ለምክክር ኮሚሽኑ “ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጥበት አግባብ” ምን እንደሆነም በወቅቱ ጠይቀዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ” የኮሚሽኑ የስራ ዘመን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ሊራዘም ይችላል” ሲል ደንግጓል። በህዳሩ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ይህንኑ ያስተጋባ ምላሽ የሰጡት ፕሮፌሰር መስፍን፤ የስራ ጊዜ የመራዘሙ ጉዳይ በምክር ቤቱ እጅ መሆኑን አስታውሰው ነበር።
“ስታቋቋሙም እናንተ ናችሁ ያቋቋማችሁት። ሶስት አመት ስሩ ብላችሁ የወሰናችሁት እናንተ ናችሁ። ከዚህ በኋላ ይብቃኝ የማለት መብት አላችሁ። ይቀጥል የማለት መብት አላችሁ። ስለዚህ እኛ ምንም ምንለው ነገር የለም” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም ኮሚሽነሮች የተቋሙን ስራዎች ለማገባደድ ከመስራት ባለፈ “ጊዜ ይራዘምልን” የሚል ጥያቄ እንደማያቀርቡ ለፓርላማ አባላት አስረድተው ነበር።
የስራ ዘመኑ ሊያበቃ አንድ ሳምንት የቀረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እና ተሳታፊዎችን የመለየት ተግባሩን በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች አጠናቅቋል። ኮሚሽኑ የጸጥታ ችግር ባለበት የአማራ ክልል በሚገኙ 259 ወረዳዎች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣን ማከናወኑንም ቢገልጽም፤ በትግራይ ክልል እስካሁን “ምንም ተግባር አለመጀመሩን” ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)