በቤርሳቤህ ገብረ
በጋምቤላ ክልል ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በተከሰተ የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ በአራት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው ወረርሽኝ፤ መነሻው በአጎራባች ከሚገኙት የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች መሆኑንም የጤና ቢሮው ገልጿል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ በላይነህ፤ ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት በአኮቦ ወረዳ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአተት ወረሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠው በዘጠኝ ሰዎች ላይ ቢሆንም፤ ከአንድ ሳምንት በኋላ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 136 መድረሱን ኃላፊው አስረድተዋል።
በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት የሚያጋጥማቸው በመሆኑ በአተት መጠቃታቸው ይገልጽ እንጂ፤ በህማሙኑ ላይ የታዩት የበሽታው ምልክቶች በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ትንታኔ መሰረት በኮሌራ መያዛቸውን የሚያመለክት መሆኑን አቶ ወንድማገኝ አብራርተዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ፤ ወረርሽኙ ኮሌራ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ናሙና ወደ አዲስ አበባ አበባ መላኩንም አክለዋል።

“እኛ ከዚህ ወደ ኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ናሙና ልከናል። ትክክለኛ ኮሌራ ነው ብሎ ማረጋገጫ አላከልንም” ሲሉ አቶ ወንድማገኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማስከትል፣ በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጥጦ በማስወጣት፣ አቅምን በማዳከም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው።
በዚሁ በሽታ ሳቢያ ካለፈው መስከረም አጋማሽ እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ፤ ከጋምቤላ ክልል ጋር በሚጎራበተው ደቡብ ሱዳን 475 ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። በዚሁ የአራት ወራት ጊዜ ውስጥ በደቡብ ሱዳን በኮሌራ የተያዙ ሰዎች ብዛት 24 ሺህ ገደማ መሆኑን ድርጅቱ ጨምሮ ገልጿል።
በጋምቤላ ክልል የተከሰተው የአተት ወረርሽኝ መነሻው ከደቡብ ሱዳን መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። “ሰዎች ከዚህም ወደዚያ፤ በተለይ ከዚያ በጣም ወደዚህ ይመጣሉ። በሰላሙም እጦት [ምክንያት] የደቡብ ሱዳን [ዜጎች] ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ሁኔታ አላቸው” ሲሉ አቶ ወንድማገኝ ድንበር ዘልል ስለሆነው ስለ ሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት አስረድተዋል።

በጋምቤላ ክልል ወረረሽኙ መጀመሪያ የተከሰተው በኑዌር ብሔረሰብ ዞን በሚገኘው አኮቦ ወረዳ ቢሆንም፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ከወረዳ ወረዳ በሚያደርጉት “እንቅስቃሴ” ምክንያት ወደ ሌሎች ቦታዎች መዛመቱን አቶ ወንድማገኝ አመልክተዋል። በዞኑ የሚገኙ የአተት ወረርሽኙ የተዛመተባቸው ዋንቱዋ፣ ማኩዌይ እና ላሬ የተባሉ ወረዳዎች ነው።
ወረርሽኙ መከሰቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ጤና ቢሮ በድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማዕከል በኩል ለህሙማን ህክምና እየሰጠ መሆኑን አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ከፌደራል የጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን መድኃኒት፣ የህክምና መገልገያ እና ለይቶ ማቆያ ቁሳቁሶችን በወረርሽኙ በተጠቁ አካባቢዎች እያደረሰ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ይህን ተከትሎም በአብዛኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች በሚገኙባቸው በአኮቦ እና በዋንቱዋ ወረዳዎች ጊዜያዊ የህክምና መስጫ መቋቋሙን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል። በላሬ እና በማኩዌይ ወረዳም በተመሳሳይ መልኩ ጊዜያዊ የህክምና ጣቢያ በቅርቡ እንደሚከፈት ቢሮው ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)