የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ “ቴክኒካዊ ድርድር” ዛሬ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አመቻችነት የሚያካሄዱት “ቴክኒካዊ ድርድር” ዛሬ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። በሶማሊያ የማስታወቂያ፣ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ ሰኞ ወደ አንካራ አቅንቷል። 

ሚኒስትሩ በኤክስ ይፋዊ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የሁለቱን ሀገራት የመጀመሪያ ዙር ቴክኒካዊ ውይይት ለማስጀመር በአንካራ የሶማሊያ ልዑካንን መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል። ዳውድ አዌይስ በዚሁ መልዕክታቸው፤ ውይይቱ “የአንካራ ቃል ኪዳንን ተግባራዊ ለማድረግ መንገዶች ለማፈላለግ” ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ልዩነቶቻቸውን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ ለመተው” እና “ትብብር ለማበጀት” በአንካራ ስምምነት የተፈራረሙት ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ሁለቱ ሀገራት በቱርክ አመቻችነት በተፈራረሙትን በዚሁ ስምምነታቸው፤ “አንዳቸው ለሌላው ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት ያላቸውን ክብር እና ቁርጠኝነት” መግለጻቸው ይታወሳል።   

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ የተፈራረሙትን ይህን ስምምነት ተከትሎ፤ ሁለቱ ሀገራት በየካቲት ወር “ቴክኒካዊ ድርድር” እንደሚያደርጉ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ቴክኒካዊ ድርድሩ የባህር በር ጉዳይን ጨምሮ በአንካራው ስምምነት የተካተቱ ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥንም በወቅቱ ተጠቅሷል። 

በአራት ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቅ እቅድ ከተያዘለት ከዚህ ድርድር በኋላ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አዲስ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚሁ ቴክኒካዊ ድርድር ላይ ለመሳተፍ አንካራ የገቡት የሶማሊያ የማስታወቂያ፣ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር፤ ሀገራቸው “በጋራ መግባባት እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ሰላም ለማስፈን፣ ትብብርን ለማጠናከር እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመገንባት ቁርጠኛ ነች” ብለዋል።  

ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የነበራቸውን ግንኙነት “ወደነበረበት ለመመለስ” የተስማሙት፤ ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ነበር። ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ  በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅትም፤ “ዳግም በቁልፍ ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ” መወያየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)