በቤርሳቤህ ገብረ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 11፤ 2017 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለአንድ አመት አራዘመ። የኮሚሽኑን የስራ ዘመን ለማራዘም የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፤ በሶስት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ በአብላጫ ጽምጽ ጸድቋል።
መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች “ወሳኝ ምክንያቶችን የመለየት” እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት “ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት” ዓላማ ይዞ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፤ በአዋጅ የተቀመጠለት የስራ ዘመን ሶስት ዓመት ነው። የተወካዮች ምክር ቤት በእረፍት ላይ ያሉትን የፓርላማ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው፤ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ከማለቁ ሁለት ቀን አስቀድሞ ነው።
ፓርላማው ኮሚሽኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በስራ ላይ እንዲቆይ ውሳኔ ከማሳለፉ አስቀድሞ፤ የተቋሙን የሶስት ዓመታት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል። ሪፖርቱን ለፓርላማ አባላት በንባብ ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ የምክክር፣ የአጀንዳ መለየት እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራዎችን በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ 124,695 ሰዎች የወረዳ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ማድረጉን በሪፖርታቸው የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ይህም ተቋሙ ከያዘው እቅድ አንጻር 75.6 በመቶውን የሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል። ከ1,231 ወረዳዎች የተመረጡት እነዚህ ተሳታፊዎች በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ለሚቀርቡ አጀንዳዎች ግብዓት በመስጠት እና በጉባኤው የሚወክሏቸውን ግለሰቦች በቃለ ጉባኤ እንዲለዩ መደረጉንም አብራርተዋል።
በአማራ ክልል በሚገኙ 259 ወረዳዎች በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ተወካዮች ቢለዩም፤ ኮሚሽኑ በቀሪ ስምንት ወረዳዎች ተመሳሳይ ክንውን ማድረግ እንደሚጠበቅበት በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል። በዚሁ ክልል አጀንዳ የሚሰባሰብበት ክልላዊ የምክክር ጉባኤ ያልተከናወነ ሲሆን፤ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ወኪሎችም ገና አልተመረጡም።
እነዚህ ሂደቶች በተመሳሳይ ሁኔታ ባልተካሄዱበት የትግራይ ክልል፤ የተባባሪ አካላት፣ የተሳታፊዎች ልየታ እንዲሁም ክልላዊ የምክክር ጉባኤ አለመከናወናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል። ኮሚሽኑ ለፓርላማ አባላት ባሰራጨው ሪፖርት ላይ ለዚህ በምክንያትነት ያስቀመጠው፤ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና በህወሓት መካከል “አለመግባባቶች” “መኖራቸውን እና መቀጠላቸውን” ነው።

ከትግራይ እና ከአማራ ክልሎች በቀጣይ በሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች እስካሁን ባይመረጡም፤ ከቀሪዎቹ ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ 1,105 ተመራጮች በጉባኤው ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ፕሮፌሰር መስፍን በሪፖርታቸው አመልክተዋል። በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ ከሚሳተፉ ተወካዮች መካከል 45.3 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ይህም ተቋሙ ካስቀመጠው የ30 በመቶ የሴቶች ተሳትፎ ግብ በላይ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ በዛሬው ሪፖርታቸው የጠቀሱት ሌላው ጉልህ ክንውን፤ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ነው። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፤ ከ1,260 በላይ “የጥቃቅን እና ንዑስ ቡድኖችን” የአጀንዳ ሰነዶች መሰባሰብ እንደቻለ በሪፖርቱ አስታውቋል። በህብረተሰብ ክፍሎች ደረጃ ኮሚሽኑ ያገኛቸው የተጠቃለሉ የአጀንዳ ሰነዶች 109 እንደሆኑም ተጠቁሟል።
ኮሚሽኑ በአጀንዳ የመለየት ሂደቱ ከተካፈሉ 55 ቡድኖች፤ “በተናጠል” የአጀንዳ ሰነዶች መሰብሰቡ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። እነዚህ አጀንዳዎች የተሰበሰቡት፤ በአስሩ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት፣ ማህበራት እና ተቋማት እንዲሁም ከወረዳ ህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እንደሆነም ተብራርቷል።

እስካሁን ከክልሎች እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተገኙ የተጠቃለሉ የአጀንዳ ሰነዶች ብዛት 11 እንደሆነም ለፓርላማ የቀረበው የኮሚሽኑ ሪፖርቱ አመልክቷል። በተለያየ መንገድ የተሰበሰቡትን እነዚህን አጀንዳዎች፤ “በየፈርጁ የማደራጀት እና ዶክመንት የማድረግ ስራ” መከናወኑ ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በአካል፣ በፖስታ፣ በኢሜይል ከተለያዩ አካላት የተቀበላቸው እና በህዝባዊ ውይይት የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን፤ “በአግባቡ ሰንዶ የማስቀመጥ”፣ “በየፈርጁ የማደራጀት” እና “ወደ ሶፍት ኮፒ በጽሁፍ የመቀየር” ተግባር በተጓዳኝ እያካሄደ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል። ኮሚሽኑ “ለሀገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ያላቸው” በሚል የገለጻቸውን፤ በተለያዩ ተቋማት የተከናወኑ ጥናቶችን የማሰባሰብ ስራ ማጠናቀቁንም አስታውቋል።
የምክክር ኮሚሽኑ በሶስት ዓመታት የስራ ዘመኑ ውስጥ ወደ ተቋሙ ለመጡ ቅሬታ እና አቤቱታዎች፤ “አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ” ምላሽ መስጠቱን በዛሬው ሪፖርቱ አመልክቷል። ለኮሚሽኑ ከቀረቡለት አቤቱታዎች መካከል ከብሔር ብሔረሰብ ኮታ ማነስ ጋር በተያያዘ የተነሱ፣ የሙስሊም ማህበረሰብ ተሳትፎን የተመለከቱ እንዲሁም “ያለ ህጋዊ ውክልና በምክክር ላይ በተጠሩ ዜጎች” የቀረቡ ቅሬታዎች ይገኙበታል።

ከክልላዊ አጀንዳ ጥንቅር ጋር በተያያዘ የቀረቡ አቤቱታዎችን እና የጸጥታ ችግርን የተመለከቱ ቅሬታዎችን በተመሳሳይ መልኩ የተቀበለው ኮሚሽኑ፤ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት “ከቅሬታ አቅራቢዎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል” ብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)