በአራት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነሳ 

በተስፋለም ወልደየስ

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “ህግን ተላልፈው ተገኝተዋል” በሚል በአራት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ጥሎት የነበረውን የእግድ እርምጃ፤ “ማስጠንቀቂያ” በመስጠት ከዛሬ ጀምሮ ማንሳቱን አስታወቀ። ባለስልጣኑ እገዳውን ያነሳው፤ ከታገዱት ድርጅቶች ጋር ባደረገው ውይይት “በተፈጠረ መግባባት” እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ አስታውቋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የዛሬውን ውሳኔ ያስተላለፈው “በታገዱት ሁሉም ድርጅቶች” ላይ መሆኑን ዛሬ ሰኞ የካቲት 24፤ 2017 ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ባለፈው መንፈቅ ዓመት ብቻ በሰባት ድርጅቶች ላይ የእግድ ውሳኔ ማስተላለፉን ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ በፓርላማ በተካሄደው የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ መግለጹ ይታወሳል።

በዚሁ ጊዜ ውስጥ ከታገዱት መካከል አራቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ናቸው። “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ የታገዱት እነዚህ ድርጅቶች፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR) ናቸው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በወቅቱ ለድርጅቶቹ በጻፈው የእግድ ደብዳቤ፤ “ኃላፊነት በጎደለው መልኩ” በመንቀሳቀስ እና “ገለልተኛ ባለመሆን” ውንጅሏቸዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሰረት ስራቸውን ማከናወናቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ባለስልጣኑ፤ በድርጅቶቹ ላይ ተጨማሪ “የማጣራት” እና “የምርመራ” ስራ እያከናወነ መሆኑን ባለፈው ወር መጨረሻ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጾ ነበር።

ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ በዛሬው መግለጫው በታገዱ ድርጅቶች ላይ ሲያደርግ የቆየውን ምርመራ ስራ “ማጠናቀቁን” ገልጿል። ይህን ተከትሎም በምርምራ ውጤቱ ላይ ከድርጅቶቹ ጋር መነጋገሩ የጠቀሰው ባለስልጣኑ፤ “መታረም የሚገባቸው እንደሚታረሙ እንዲሁም በቀጣይ በቅንጅትና ትብብር ለመስራት የጋር መግባባት መፍጠር ተችሏል” ብሏል።

እግዱን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አመራሮች ጋር “ምክክር” መደረጉን የጠቆመው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ በኮሚሽኑ በኩል የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች እገዳውን ለማንሳት “ከግምት ውስጥ” መግባታቸውን አመልክቷል። ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ኢሰመኮ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ በድርጅቶቹ እገዳ ላይ “ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ማከናወኑን” እና “የደረሰባቸውን ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች” ለሚመለከታቸው አካላት ማጋራቱን አረጋግጧል። 


ኢሰመኮ በአዲሱ ዋና ኮሚሽነሩ አቶ ብርሃኑ አዴሎ በኩል ጉዳዩን “በልዩ ትኩረት ሲከታተል” እና ለእገዳው “መፍትሔ ለማስገኘት ሲሰራ” መቆየቱን በመግለጫው አስታውሷል። የኮሚሽኑ ጥረት “ውጤት በማስገኘቱ”፤ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ በሚሰሩ አራት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ከዛሬ ሰኞ የካቲት 24፤ 2017 ጀምሮ በመነሳቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

የሚከሰቱ ችግሮችን “የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ” እና “ሀገራዊ ጥቅምን በማስቀደም”፤ “በመቀራረብ እና በመወያየት” የመፍታት ልምድ እንዲጎለብት ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው ጥሪውን አቅርቧል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በበኩሉ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች “የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ” “በኃላፊነት ስሜት” እና “ገንቢ በሆነ ትብብር” እንዲጠቀሙ አሳስቧል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች “በተቋቋሙበት አላማ መሰረት፣ ገለልተኛነታቸውን በመጠበቅና በህግ አግባብ በመንቀሳቀስ የሀገር እና የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መስራት የሚገባቸው መሆኑን እናሳስባለን” ሲል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዛሬው መግለጫ አጽንኦት ሰጥቷል። ከዚህ አኳያም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የጀመረውን የክትትል እና የቁጥጥር ስራ “አጠናክሮ የሚቀጥል” መሆኑንም አስታውቋል።

“የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተቋቋሙበት አላማ መሰረት፣ ገለልተኛነታቸውን በመጠበቅና በህግ አግባብ በመንቀሳቀስ የሀገር እና የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መስራት የሚገባቸው መሆኑን እናሳስባለን”

– የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን

ባለፈው ታህሳስ ወር እገዳ የተጣለባቸው ድርጅቶች፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለእግድ በምክንያትነት የጠቀሳቸው ምክንያቶች “ከእውነታው የራቁ” መሆናቸውን በወቅቱ ገልጸው ነበር። ከድርጅቶቹ አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ስራውን “በፍጹም ገለልተኝነት፣ “ኃላፊነት በተሞላበት ጥንቃቄ” እና “የድርጅቱን መርሆዎች በተከተለ መልኩ ብቻ ሲያከናወን” መቆየቱን እገዳውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል በበኩሉ “ግልጽነት”፣ “ገለልተኝት” እና “ዴሞክራሲያዊነት” የማያወላውል መርሆዎቹ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ድርጅቱ “ከዓላማው ውጪ ምንም ዓይነት ተግባራት ላይ እንደማይሳተፍ” እና “በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ፍጹም ገለልተኛ ተቋም መሆኑን” በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።

አንጋፋው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም (ኢሰመጉ) ከእግዱ በኋላ በተመሳሳይ መልኩ ባወጣው መግለጫ፤ “ህግ እና ስርዓትን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ፣ ነጻ እና ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ድርጅት መሆኑን” መግለጹ አይዘነጋም ነበር። በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ እና በመሰነድ የሚታወቀው ኢሰመጉ፤ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አማካኝነት ከተመሰረተበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ የቆየ ድርጅት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]