የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን ለማቋቋም ያወጣውን “ልዩ መመሪያ” የተፈጻሚነት ጊዜ በድጋሚ ለአንድ ዓመት አራዘመ 

በቤርሳቤህ ገብረ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “በሰላም የተመለሱ” የቀድሞ ታጣቂዎች ለማቋቋም ያወጣውን “ልዩ መመሪያ” ተግባራዊ የሚደረግበትን የጊዜ ወሰን ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዘመ። የመመሪያው የተፈጻሚነት ጊዜ የተራዘመው፤ የተደራጁ የቀድሞ ታጣቂዎች “ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ” እና ቀሪዎቹ “እንዲደራጁ ለማስቻል ነው” ተብሏል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “የሰላም ተመላሾችን ለማቋቋም” እና “ወደ ስራ ለማስገባት” ያለመ “ልዩ መመሪያ” ያጸደቀው በየካቲት 2015 ዓ.ም ነበር። ልዩ መመሪያው የሚመለከተው፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች “ህገ መንግስታዊ ስርዓትን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ” እና “መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተረድተው የመጡ” “ኃይሎችን” እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።

የአንድ አመት የተፈጻሚነት ጊዜ ተሰጥቶት የነበረው ይህ መመሪያ፤ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  ካቢኔ ከጸደቀ ከአምስት ወራት በኋላ እንደነበር በክልሉ የሰላም ተመላሾች ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ባለሙያ የሆኑት አቶ ምግባሩ ታደሰ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መመሪያው ተግባራዊ የሚደረግበት ጊዜ ከዚህ ቀደም እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም እንዲራዘም ተደርጎ ነበር። 

ፎቶ፤- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት

ይህ የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ሶስት ወራት ሲቀረው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ የመመሪያው የተፈጻሚነት ወሰን በድጋሚ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም አድርጓል። የክልሉ ካቢኔ ውሳኔውን ያሳለፈው ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 13፤ 2017 ባደረገው ስብሰባ ነው። 

የካቢኔው አባል የሆኑት የክልሉ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሰላም ሸንገል፤ የመመሪያው የጊዜ ወሰን እንዲራዘም ከተደረገበት ምክንያት አንዱ “በራሳቸው ምክንያት መደራጀት ያልቻሉ” የቀድሞ ታጣቂዎችን እንዲደራጁ ለማስቻል እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የጊዜ መራዘሙ “ተደራጅተው ስራ ያልጀመሩ” የሰላም ተመላሾችን ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚያደርጋቸውም ጠቁመዋል። 

“ ‘ተደራጅተዋል’ በሚል ሜዳ ላይ ተበትነው እንደገና ወደ ችግር ከሚመለሱ፤ [የሰላም ተመላሾች ጊዜያዊ] ጽህፈት ቤቱን እንዲደግፋቸው እና ውጤታማ ስራ እንዲሰሩ ነው ለአንድ አመት የተራዘመው” ሲሉ አቶ አብዱሰላም ውሳኔው የተላለፈበት ምክንያትን አብራርተዋል። የሰላም ተመላሾች “የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ” የተቋቋመው ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት፤  ባለፈው በጀት ዓመት 7,625 አባላት በስራቸው ላሏቸው 395 ኢንተርፕራይዞች ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

ፎቶ፦ የመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ

በዘንድሮው በጀት ዓመት በ10 ኢንተርፕራይዝ ስር ለተደራጁ የሰላም ተመላሾች አራት የወርቅ መፍጫ ማሽን እንደተሰጣቸው እና በመጪዎቹ ወራት ተጨማሪ ሶስት ማሽኖች ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። በ194 ኢንተርፕራይዞች በአገልግሎት ዘርፍ የተደራጁ 1,317 የሰላም ተመላሽ አባላት ስራ ቢጀምሩም እስካሁን ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው በመስሪያ ቤቱ የአደረጃጀት ባለሙያ የሆኑት አቶ ምግባሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ ያላገኙት “በበጀት እጥረት ምክንያት” እንደሆነ አቶ ምግባሩ አክለዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካቢኔ ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ባደረገው ስብሰባ፤ ካቢኔ ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለተመለሱ እና በጸጥታ መደፍረስ ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማቋቋም የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፎ ነበር። 

ኮሚቴው የቀድሞ ታጣቂዎችን እና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም፤ በዚህ አመት እንዲያሰባስብ የታቀደው የገንዘብ መጠን 130 ሚሊዮን ብር ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ፣ የሰላም ተመላሽ ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸውን መልሶ ለማቋቋም፤ 90 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የአሶሳ ዩኒቨርስቲ ያጠናው አንድ ጥናት ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)