ከ47 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮንን መግዛታቸውን ኩባንያው አስታወቀ

በቤርሳቤህ ገብረ

ኢትዮ ቴሌኮም ለህዝብ ሽያጭ ካቀረበው 10 በመቶ ድርሻ፤ ከ47 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ዜጎች አክሲዮን መግዛታቸውን አስታወቀ። በዲጂታል መንገድ ብቻ በተከናወነው በዚህ የአክሲዮን ሽያጭ፤ ኩባንያው 3.2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት ማሰባሰቡንም ይፋ አድርጓል። 

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ተቋም፤ ኩባንያው የ10 በመቶ ድርሻውን በይፋ ለህዝብ መሸጥ መጀመሩን ይፋ ያደረገው ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ነበር። ኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ሽያጩን ከመጀመሩ አስቀድሞ፤ ተቋሙን ከልማት ድርጅትነት ወደ አክሲዮን ማህበርነት በመቀየር በንግድ ህጉ መሰረት በሰኔ 2016  ዓ.ም. አጋማሽ  ምዝገባ አድርጓል።  

ኩባንያው የአክሲዮን ሽያጩን ላለፉት 121 ቀናት ሲከናወን የቆየ ሲሆን ሂደቱን በተመለከተ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል  መግለጫ ሰጥቷል። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባቀረቡት ማብራሪያ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ 10.7 ሚሊዮን የኩባንያው መደበኛ አክሲዮኖች መሸጣቸውን አስታውቀዋል።

አክሲዮኖቹን የገዙት “በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች” ብዛት 47,377 መሆናቸውንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። የአክሲዮን ሽያጩ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን መጽደቅ እንደሚገባው ፍሬህይወት በዚሁ ማብራሪያቸው ላይ ተናግረዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም በመጀመሪያ ዙር ለሽያጭ ያቀረባቸው መደበኛ አክሲዮኖች ብዛት 100 ሚሊዮን ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው 300 ብር ዋጋ ያላቸው ነበሩ። የኩባንያውን አክሲዮን መግዛት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ እስከ 3,333 አክሲዮን ድረስ መግዛት እንደሚችል በወቅቱ ተገልጿል። ኢትዮ ቴሌኮም ለሽያጭ ያቀረበው ዝቅተኛው የአክሲዮን መጠን 33 ነው።

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከ3,001 እስከ 3,333 የሚሆነውን ከፍተኛ የአክሲዮን መጠን የገዙት 712 ኢንቨስተሮች መሆናቸው ተገልጿል። ከአክሲዮን ገዢዎች መካከል 30,014 የሚሆኑት የገዙት አክሲዮን ከ33 እስከ 100 የሚሆን መጠን ያለው እንደሆነም ዛሬ ይፋ ተደርጓል።


በዚህም መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ለሽያጭ ካቀረባቸው አክሲዮኖች ውስጥ 89.3 ሚሊዮን ያህሉ እስካሁንም አልተሸጡም። የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ የቀሩትን አክሲዮኖች ሽያጭ በሚመለከት፤ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና “በየደረጃው ካሉ የመንግስት ባለስልጣናት እና ውሳኔ ሰጪ አካላቶች ጋር” ውይይት እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

“ሂደቱ አልተጠናቀቀም። በዚህ ሂደት እየተመለከትን ያለነው፤ በመጀመሪያው ሂደት ላይ ለመሳተፍ የፈለጉ በደብዳቤም ጭምር [የጠየቁ] ኩባንያዎች አሉ። ባንኮችን ጨምሮ ሼር ከኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮን ድርሻ መግዛት የሚፈልጉ አሉ። እንደዚሁም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ አቅርበዋል” ሲሉ ፍሬህይወት በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ መልኩ የቀረቡለትን ጥያቄዎች ታሳቢ በማድረግ እና መንግስት በጉዳዩ ላይ ወደፊት በሚሰጠው አቅጣጫ ላይ በመመርኮዝ፤ ቀጣይ የአክሲዮኖች ሽያጭ የሚካሄድበትን ጊዜ እንደሚያሳውቅ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል። መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅራቢ በአጠቃላይ ያለው የመደበኛ አክሲዮኖች ብዛት አንድ ቢሊዮን እንደሆነ ባለፈው ጥቅምት ወር አስታውቆ ነበር። 

ኩባንያው ከመጀመሪያው ዙር የአክሲዮን ሽያጭ 30 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቢያቅድም፤ እስካሁን ባለው ሂደት ግን ያሳካው 3.2 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ኢትዮ ቴሌኮም በቀጣይ ከሚያከናውናቸው ስራዎች ውስጥ ኩባንያውን በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ማስመዝገብ ይገኝበታል። ይህ ሂደት የኢትዮ ቴሌኮም አክሲዮኖች በሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ ለሽያጭ እንዲቀርቡ ያስችላል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]