በቤርሳቤህ ገብረ
የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር በክልሉ ለሚገኙ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጭማሪ ተፈጻሚ ሳይሆን በመዘግየቱ “ከፍተኛ ቅሬታ” ማስነሳቱን ገለጸ። ለደመወዝ ጭማሪው የሚያስፈልገውን በጀት የአማራ ክልል መንግስት እንዲመድብ ለማድረግ፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “የቅርብ ክትትል እና ጥረት” እያደረገ መሆኑን ማህበሩ አስታውቋል።
የዳኞች ማህበሩ ይህን ያስታወቀው ትላንት እሁድ ሚያዝያ 19፤ 2017 ለአባላቱ ባስተላለፈው መልዕክት ነው። ማህበሩ በዚሁ መልዕክቱ፤ ፍርድ ቤቶችን ከማጠናከር እና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጀመረውን የለውጥ ስራ የተሟላ ከማድረግ አኳያ የዳኞችን እና የጉባኤ ተሿሚዎችን ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻሉ “የማይተካ ሚና ያለው” “መሰረታዊ ነጥብ” እንደሆነ አስገንዝቧል።
የዳኞች ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄን ለመመለስ፤ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮሚቴ አዋቅሮ ጥናት ካደረገ በኋላ በክልሉ ዳኞች አስተዳደር ዐብይ ጉባኤ አማካኝነት ዝርዝር መመሪያ ማጽደቁን ማህበሩ አስታውሷል። በ2014 ዓ.ም. የወጣው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች አስተዳደር ጉባኤን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ የደመወዝ፣ የእረፍት እና የጥቅማ ጥቅም አይነት እና ደረጃ እንዲሁም መሰላል የመወሰን እና መመሪያ የማውጣት ስልጣን ለዐብይ ጉባኤው ይሰጣል።

ዐብይ ጉባኤው ካጸደቀው የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም በተጨማሪ ሀገር አቀፍ የኑሮ ውድነት ማሻሻያ የደመወዝ ጭማሪ ለሁሉም ሰራተኛ የተደረገ መሆኑን በትላንቱ መልዕክቱ የጠቀሰው ማህበሩ፤ ሁለቱም “እስካሁን ተፈጻሚ ባለመሆናቸው” በዳኞች ዘንድ “ከፍተኛ ቅሬታ” እያስነሳ መሆኑን ገልጿል። የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር የትላንቱን መግለጫ ያወጣው፤ ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ በርካታ ዳኞች ጥያቄ በማቅረባቸው “ያለበትን ሂደት ለማሳወቅ” እንደሆነ የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ አሰፋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዳኞች ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም የሚያስፈልገውን የበጀት መጠን ጠቅሶ፤ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ ለክልሉ ምክር ቤት እና ለክልሉ ገንዘብ ቢሮ ማሳወቁን ማህበሩ አመልክቷል። አዲስ የጸደቀው የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም መመሪያ የትራንስፖርት፣ የቤት ኪራይ፣ የአልጋ እና የካርድ አበልን እንደሚያካትት የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ “ውሳኔው የሚፈጸመው የክልሉ መንግስት በጀት ሲበጅት ነው። ስለዚህ በጀቱ እንዲመደብ ጥያቄ ቀርቦ በመጠበቅ ላይ ነን” ሲሉ ያለበትን ሂደት አስረድተዋል።
በአማራ ክልል የሚገኙ ዳኞች ለመጨረሻ ጊዜ የደመወዝ ጭማሪ የተደረገላቸው ከአምስት አመት በፊት እንደነበር የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አስታውሰዋል። በወቅቱ የተደረገው የደመዝ እድገትም ከ80 አስከ 82 በመቶ ጭማሪ የታየበት እንደነበርም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት እየተከፈለ የሚገኘው ያልተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ፤ ለወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች 15 ሺህ ብር ገደማ፣ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች 19 ሺህ ብር ገደማ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች 23 ሺህ ብር ገደማ እንደሆነ አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል።

የሚከፈላቸው የተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ 15,400 ብር እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት የሚያገለግሉት አቶ አያሌው ነብዩ፤ በሚያገኙት ደመወዝ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። በዳኝነት ለአስር አመት የሰሩት አቶ አያሌው፤ እስካሁን ድረስ የደመወዝ ጭማሪ የተደረገላቸው ሁለት ጊዜ መሆኑን ያስረዳሉ።
“የደረጃ እድገት የለም። ዛሬ የገባ ሰው ሁለት አመት ሶስት አመት ልምድ ካገኘ በኋላ ወደ ጥብቅና እንዲወጣ የሚያደርገው፤ የመቆየት value የሚያሳጣ ስለሆነ ነው” ሲሉ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛው ይገልጻሉ። እርሳቸው በተመደቡበት ፍርድ ቤት በየጊዜው ዳኞች ስራቸው እንደሚለቅቁ የሚናገሩት አቶ አያሌው፤ ለዚህ አንደኛው ምክንያት የደመወዝ ክፍያው አነስተኛነት ነው ባይ ናቸው።
የአማራ ክልል ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው የካቲት ወር ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፤ በዚህ ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 89 ዳኞች መልቀቃቸውን አስታውቆ ነበር። አቶ አያሌው “በዳኝነቱ ተከብሮ የሚኖር፣ ፍትህ መስጠት የሚችል ሰው፣ መቋቋም አቅቶት የሚለቅ ነው” ሲሉ የደመወዝ ክፍያው ከኑሮ ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ምክንያት ዳኞች ከስራቸው እንደሚለቅቁ ያብራራሉ።
“ስለሚለብሰው ስለሚመገበው ነገር ተሳቅቆ፣ መኖሪያው በከተማ ተከራይቶ በማይችል፣ እራሱን አደጋ ላይ በሚጥል መንገድ ከሆነ፤ ነገ ሀገር፣ ፍትህ ስለ ሚባለው ነገር [ቀርቶ] ስርአተ መንግስትም በደንብ መስርቶ ለመቀጠል፣ ለማሰብ ከባድ ነው የሚያደርገው”
– አቶ አያሌው ነብዩ፤ የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ
“ስለሚለብሰው ስለሚመገበው ነገር ተሳቅቆ፣ መኖሪያው በከተማ ተከራይቶ በማይችል፣ እራሱን አደጋ ላይ በሚጥል መንገድ ከሆነ፤ ነገ ሀገር፣ ፍትህ ስለ ሚባለው ነገር [ቀርቶ] ስርአተ መንግስትም በደንብ መስርቶ ለመቀጠል፣ ለማሰብ ከባድ ነው የሚያደርገው” ሲሉ ለጉዳዩ በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ። የአማራ ክልል ዳኞች ማህበርም በትላንቱ መግለጫው፤ የዳኞች የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ “አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጫና አኳያ” “ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልገው” እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቷል።
የአማራ ክልል የመንግስት አካላት ለዚህ የሚያስፈልገውን በጀት “ፈጥኖ በመመደብ”፤ “ለፍርድ ቤቶች መጠናከር የተለመደውን ትብብራቸውን” እንዲያደርጉ ማህበሩ ጠይቋል። የማህበሩ አባል ዳኞችም በጀት በማስመደብ ሂደት ውስጥ የሚወስደውን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ፤ በትዕግስት እንዲጠባበቁ አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)