በቤተልሔም ሠለሞን
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፤ የፋይናንስ አቅርቦት “መሰረታዊ ችግር” እንደሆነ ተገለጸ። የማስፈጸም አቅም ውስንነት እና በቅንጅት አለመስራት ኢንተርፕራይዞቹ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለመፍታት ተግዳሮት መሆናቸውም ተነግሯል።
ይህን የገለጸው የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን የመደገፍ፣ የማስፋፋት እና የማሸጋገር ስራዎችን እንዲሰራ በ2015 ዓ.ም. በአዲስ መልክ የተደራጀው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ተቋም ነው። ተቋሙ ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 20፤ 2017 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 518 አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ያጋጠማቸውን ችግር በመፍታት ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረጉን አስታውቋል።
መግለጫውን የሰጡት የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዱልፈታ የሱፍ፤ በዚሁ ጊዜ ውስጥ 2,752 አዳዲስ አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ማቋቋም መቻሉን ተናግረዋል። በመስሪያ ገንዘብ እጥረት ምክንያት አምራች ኢንተርፕራይዞች “በበቂ ደረጃ” ወደ ስራ አለመግባታቸውንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

አምራች ኢንተርፕራይዞቹ ለስራ የሚያስፈልጋቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ከንግድ ባንኮች ለማግኘት በሚጠይቁበት ወቅት፤ የብድር ዋስትና ማስያዣ እንዲያቀርቡ የሚጠየቁ መሆኑ መሰረታዊ ችግር እንደሆነም አቶ አብዱልፈታ አብራርተዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ተቋሙ ለ1,209 አምራች ኢንተርፕራይዞች ከ6 ቢልየን ብር በላይ የስራ ማስኪያጃ ብድር መስጠቱንም አስረድተዋል።
ተቋሙ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሩን በዚህ መልኩ ለመፍታት ጥረት ቢያደርግም፤ አምራች ኢንተርፕራይዞች በመስሪያ ቦታ እጥረት ምክንያት መቸገራቸውን ገልጸዋል። ተቋሙ ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት፤ የመስሪያ ቦታዎች “በክላስተር” ሆነው በግል ዘርፍ እንዲለሙ የማድረግ አካሄድን መከተል መጀመሩን ጠቁመዋል።
አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለማቃለል በተቋማት መካከል “የቅንጅት ክፍተት” እንደሚስተዋልም አቶ አብዱልፈታ አስረድተዋል። “ይህ ስራ የሚሰራው በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ነው። ፋይናንስ የሚቀርበው በፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ነው። መሬት የሚቀርበው በመሬት አቅራቢ ተቋማት ነው። የተለያየ የአቅም ግንባታ ስልጠና የሚሰጠው በሌላ አካል ነው። እነዚህ አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ በማድረግ የቅንጅት ውስንነት አለ” ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ በ“ኢትዮጵያ ታምርት” ኢኒሼቲቭ፤ በቅንጅት ሊሰሩ ለሚችሉ የተለያዩ ተቋማት “የክላስተር አደረጃጀት” መፈጠሩንም አቶ አብድልፈታ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ታምርት” የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት “ለዘርፉ ዘላቂ ልማት እና ተወዳዳሪነት” ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እየተካሄደ ያለ ንቅናቄ ነው። የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ተቋም ተጠሪነቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)