ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የ14 ሀገራት ኤምባሲዎች፤ በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ላይ ያለው “ከፍተኛ ጫና” መቀጠሉ እንደሚያሳስባቸው ገለጹ። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ በበኩሉ የፕሬስ ነጻነት አለመኖር “መረጃ የማግኘት መብትን እና የመተቸት ነጻነትን ያጓድላል” ብሏል።
ኤምባሲዎቹ እና የአውሮፓ ህብረት ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት በመላው ዓለም የሚከበረውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በማስመልከት በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ ነው። ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኒውዚላንድ የተካተቱበት የ14 ሀገራት ስብስብ፤ በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም ነጻ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ገለልተኛ ጋዜጠኝነት አስፈላጊነትን በመግለጫቸው አስታውሰዋል።
በመላው ዓለም ለሚገኙ ጋዜጠኞች ነጻነት እና ደህንነት መጠበቅ ያላቸውን ድጋፍ የገለጹት ሀገራቱ፤ በኢትዮጵያ አስተውለናዋል ያሉትን ወቅታዊ ሁኔታም አንስተዋል። በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ላይ ያለው “ከፍተኛ ጫና” መቀጠሉን እንዳስተዋሉ የጠቀሱት ሀገራቱ፤ ይህ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸውም በመግለጫቸው አስፍረዋል።

በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ጋዜጠኞች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እና የፕሬስ ነጻነት ሊከበር እንደሚገባም ሀገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫቸው ላይ አሳስበዋል። እንደ ፕሬስ ነጻነት ሁሉ የፖለቲካ እና የሲቪክ ምህዳር ክፍት መሆኑ፤ ነጻ እና የበለጸገ ማህበረሰብን ለመገንባት ቁልፍ መሆኑንም ሀገራቱ አንጽኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ በዛሬው ዕለት ያወጣው መግለጫም ይህንኑ አስተጋብቷል። የፕሬስ ነፃነት እና በቂ መረጃ ያለው ህዝብ መኖር “ለነጻ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ሁሉን አቀፍ ማህበረሰብ ቁልፍ ናቸው” ብሎ የአውሮፓ ህብረት እንደሚያምን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተላቸው የልማት ግቦችን እና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማሳካት “የፕሬስ ነፃነት ትልቅ ሚና ይጫወታል” ያለው ተልዕኮው፤ የፕሬስ ነጻነት እጦት “መረጃ የማግኘት መብትን እና የመተቸት ነጻነትን” እንደሚያጓድል አመልክቷል። “በከፍተኛ ስጋት ውስጥ” ሆኖ የሚከናወን ነጻ እና ገለልተኛ ጋዜጠኝነትን “ለመከላከል” የአውሮፓ ህብረት አሁንም ቁርጥኝነት ያለው መሆኑንም መግለጫው አትቷል።

በሁለት መግለጫዎች የተነሳው አሳሳቢው የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ፤ በትላንትናው ዕለት ይፋ በተደረገው የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ዝርዝር ላይ ይበልጥ ተንጸባርቋል። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (RSF) በዓመቱ በሚያወጣው በዚህ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ ዓምና ከነበረችበት 141ኛ ደረጃ ወደ 145ኛ ወርዳለች።
የ180 ሀገራት የፕሬስ ነጻነት በተመዘነበት በዚህ ዝርዝር፤ ኢትዮጵያ ዘንድሮም “በጣም አሳሳቢ” ከሚባለው ምድብ ውስጥ መውጣት አልቻለችም። በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ ሀገራት የጋዜጠኝነት ሙያን መተግበር “አደገኛ የሆነባቸው” አሊያም ደግሞ የፕሬስ ነጻነት “ከእነአካቴው የሌለባቸው” እንደሆኑ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)