በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ጎራ መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች፤ ፓርቲው ዳግም ምዝገባ እንዲያካሄድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ትእዛዝ በመኮንን፤ ህጋዊ ሰውነቱ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እንዲመለስለት ጠየቁ። እነዚሁ አመራሮች በክልሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትን ያቀፈውን የጊዜያዊ ምክር ቤት ህልውና እንደማይቀበሉትም አስታውቀዋል።
የፓርቲው አመራሮች ይህን ያስታወቁት፤ ከሐሙስ ሚያዝያ 23 ጀምሮ በመቐለ ከተማ በሚገኘው የሰማእታት ሃውልት አዳራሽ ሲያካሄዱት የቆዩትን ስብሰባ በትላንትናው ዕለት ሲያጠናቀቁ ባወጡት የአቋም መግለጫ ላይ ነው። “ብሔራዊ አንድነታችን ሉአላዊነታችን ለማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ ስብሰባ፤ 1,337 የፓርቲው መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል ተብሏል።
በስብሰባው ላይ ባለፈው ነሐሴ ወር በተካሄደ አወዛጋቢ የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ዶ/ር ደብረጽዮን፣ የምክትል ሊቀመንበርነት ቦታ የያዙት አቶ አማኑኤል አሰፋ፣ የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊነትን የተረከቡት ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔርን (ሞንጆሪኖ) ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል። የስብሰባው ተሳታፊዎች በስብሰባቸው ማጠቃለያ ባወጡት ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ የህወሓት የህጋዊ ሰውነት የማግኘት ጉዳይ ነው።

ህወሓት 50 ዓመት የሞላው እና “በህዝቡ ልብ የታተመ” መሆኑን በመግለጫቸው የጠቆሙት አመራሮቹ፤ የፓርቲው እውቅና “በትግራይ ህዝብ የሚወሰን ነው ብለን እናምናለን” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል። ከፕሪቶሪያ ስምምነት በተቃራኒ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን በድጋሚ ለመመዝገብ የሚያደርገውን ተደጋጋሚ ሙከራ እንደሚያወግዙም አመራሮቹ በአቋም መግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።
ምርጫ ቦርድ “ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን” ማረጋገጡን በመጥቀስ ህወሓትን ከፓርቲነት የሰረዘው በጥር 2013 ዓ.ም. ነበር። ሆኖም ቦርዱ ከፌደራል መንግስት የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ፤ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ህወሓትን በክልላዊ ፓርቲነት በድጋሚ መዝግቦታል።
ህወሓት በምርጫ ቦርድ እንዲመዘገብ የተደረገው፤ “በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ” የፖለቲካ ፓርቲዎች “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገቡ የሚያስችል ህግ በግንቦት 2016 ዓ.ም በፓርላማ መጽደቁን ተከትሎ ነው። ቦርዱ ለህወሓት የሰጠው የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ፤ የህወሓትን የቀድሞው ህልውናው “ወደነበረበት የማይመልስ” በመሆኑ እንደማይቀበለው የገለጸው በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ጎራ፤ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ የአመራሮች ምርጫ አካሄዷል።

ለጠቅላላ ጉባኤው እና በስብሰባው ላይ ለተላለፉ ውሳኔዎች እውቅና እንደማይሰጥ የገለጸው ምርጫ ቦርድ፤ ህወሓትን ለሶስት ወራት “በምንም አይነት” ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፍ አግዶታል። ህወሓት ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት የካቲት ወር ጀምሮ ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ የሚያስችል “የእርምት እርምጃ” ካልወሰደ፤ የፓርቲው ምዘገባ በቀጥታ እንደሚሰረዝም ቦርዱ ማስታወቁ ይታወሳል።
የህወሓት መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች በትላንቱ የአቋም መግለጫቸው፤ ምርጫ ቦርድ የፕሪቶሪያ ስምምነትን በመጻረር ጉዳዩን ወደ “ተራ ቴክኒካዊ ጉዳይ አውርዶታል” ሲል ነቅፈዋል። የህወሓት ህጋዊ ሰውነት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ወደነበረበት እንዲመለስም ጠይቀዋል።
አመራሮቹ በዚሁ የአቋም መግለጫቸው የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት የአፈጻጸም ሂደትንም ዳስሰዋል። “የፌደራል መንግስት ለስምምነቱ ትግበራ ቁርጠኛ አልሆነም” ሲሉ ከዚህ ቀደምም በህወሓት በኩል ሲንጸባረቅ የቆየውን አቋም ያስተጋቡት አመራሮቹ፤ “አደራዳሪዎችም ትጥቅ ፍቱ ከማለት ውጭ ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ያሳዩት ዝግጁነት ውሱን ነው” ሲሉ ተችተዋል።

በዚህም ምክንያት በመጠለያ ጣቢያዎች፣ በስደት እና “በወራሪ ኃይሎች” ስር ያለው የትግራይ ህዝብ፤ “በበሽታ እና በሞት እየተሰቃዩ ይገኛሉ” ብለዋል አመራሮቹ። ህዝቡ እነዚህን ችግሮ “መታገስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል” ሲሉም የሁኔታውን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥተዋል። በዚህ ረገድ ያለውን “መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር በመፍታት”፤ “የትግራይ ህገ-መንግስታዊ ሉዓላዊነት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት መመለስ አለበት” ሲሉም አመራሮቹ አቋማቸው አስታውቀዋል።
የህወሓት መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች በአቋም መግለጫቸው ያነሱት ጉዳይ፤ በክልሉ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባል የሆኑበትን “የጊዜያዊ ምክር ቤት” ህልውና ነው። የምክር ቤቱ መቋቋም “የህዝብን ህገ መንግስታዊ ስልጣን የሚጥስ፣ ህዝብን ያላሳተፈ፣ ትልቅ የግልጽነት ችግር ያለበት፣ በገዢ ኃይል በህዝባችን ላይ የተጫነ ነው” ሲሉ አመራሮቹ ነቅፈውታል።
ጊዜያዊ ምክር ቤቱን “ጸረ-ህገ መንግስት እና ጸረ-ዲሞክራሲ” ሲሉ የጠሩት አመራሮቹ፤ በዚህ ምክንያት ምክር ቤቱ “ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲሉ ተቃውመውታል። በክልሉ የተመረጠ መንግስት እንዲኖር እንዲሁም በትግራይ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌደራል መንግስት እና የፖለቲካ ኃይሎች በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ አመራሮቹ ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)