ከማንኛውም የውጭ ኃይል የሚደረግ “አላማው እና ስትራቴጂካዊ ስልቱ ያልታወቀ” ግንኙነት “ተቀባይነት የለውም” ሲል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጸ። ይህን መሰሉ ግንኙነት፤ የትግራይ ክልልን “መንግስት አልባ የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው” ሲልም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አቋሙን አስታውቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ያስታወቀው፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በትግራይ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በኩል ዛሬ ከሰዓት ባወጣው መግለጫ ነው። የትግራይ ህዝብ “ህልውናውን እና ብሔራዊ ጥቅሙን” ለማረጋገጥ “ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እያካሄደ” መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ ዋናው ጥያቄው የፕሪቶሪያ ስምምነት “ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ይደረግ” የሚል እንደሆነ አስገንዝቧል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በጥቅምት 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት የፈጠረውን ዕድል ተፈጻሚ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም ቢሮው በመግለጫው ላይ አመልክቷል። የትግራይ ህዝብን “ጥቅሞችን እና መብቶች ለማስከበር” እንዲሁም “ከጦርነት ስጋት እንዲጠበቅ ለማድረግ” ጊዜያዊ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑንም ቢሮው አክሏል።
ከፌዴራል መንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም ኃይል ጋር የሚኖሩ ልዩነቶች ለመፍታት፤ “በሰላማዊ” እና “ህጋዊ መንገድ” “የተቻለውን ሁሉ ጥረት” ማድረግ ተገቢ መሆኑንም መግለጫው አትቷል። ሆኖም “አላማው እና ስትራቴጂካዊ ስልቱ ያልታወቀ”፤ ከማንኛውም የውጭ ኃይል ጋር የሚደረግ ግንኙነት “ተቀባይነት እንደሌለው” ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።
“ከመርሆዎች እና እምነቶች ውጭ ያሉ ማናቸውም የውጭ ግንኙነቶች፤ ስህተት ብቻ ሳይሆን አደገኛም ናቸው” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዛሬው መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በአሁኑ ወቅት እየመሩ የሚገኙት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ፤ ስልጣኑን በተረከቡበት ስነ ስርዓት ላይ የፈረሙት “የቃል ኪዳን ሰነድ” እነዚህን መሰል ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ የሚያስገድድ ነው።
ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ የተፈረመው ይኸው ሰነድ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ከህገ መንግስታዊ፣ ከህጋዊ ስርዓት፣ ከሀገር ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶሪያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ” ሊፈጽማቸው ከሚገባቸው ተልዕኮዎች መካከል አንዱ መሆኑን ዘርዝሯል። ይህ ስምምነት በተፈረመ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለሚመራው የህወሓት ጎራ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቅ አክቲቪስት፤ “የኤርትራ መንግስት ፕሮፖጋንዳዎችን እንደሚያስተጋባ” ከሚነገርለት አርቲስት ጋር በአካል መገናኘቱ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

አወል ሲዒድ ከተሰኘው ኤርትራዊ አርቲስት ጋር የተገናኘው የትግራይ አክቲቪስት፤ “ሰብ ዝሰኣነ ሰብ” (ልፍዓተይ ተስፋ) በሚል ስያሜ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በሚያቀርባቸው “አወዛጋቢ ሃሳቦች” የሚታወቀው ብርሃነ ገብረገርግስ ነው። በዛላንበሳ ከተማ የተቀረጸ መሆኑን የተነገረለት በብርሃነ እና በአወል መካከል የተካሄደው ቃለ መጠየቅ፤ ሌተናል ጄነራል ታደሰ የፈረሙትን “የቃል ኪዳን ሰነድ የሚጥስ ነው” የሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።
ቃለ መጠየቁን ያደረገው ብርሃን፤ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ቦንብ መፈንዳቱን በመግለጽ ድርጊቱ “የግድያ ሙከራ“ መሆኑን በመጥቀስ ውንጀላ አቅርቧል። ይህን ተከትሎ በትላንትናው ዕለት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ብርሃነ፤ ዛሬ ሐሙስ መፈታቱ ተገልጿል። የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ በፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ ብርሃንን በቁጥጥር ስር ያዋለው “ህጋዊ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት“ እንደሆነ ገልጿል።
ብርሃነ የተያዘው “የተጠረጠረበትን ወንጀል ለማጣራት” እንደነበር የገለጸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ሆኖም ምርመራውን እንዳያካሄድ በደረሰበት “ከአቅም በላይ የሆነ ጫና” ምክንያት ተጠርጣሪውን ለመልቀቅ መገደዱን አስታውቋል። ኮሚሽኑ “ተቋማዊ ነጻነቴን ጠብቄ ምርመራዬን እንዳልቀጥል አድርገውኛል” ያላቸውን አካላት ማንነት ከመግለጽ ተቆጥቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)