ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ኪሳራ ቢያጋጥመውም፤ በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ ትርፋማነት ይሸጋገራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የእናት ኩባንያው ኃላፊዎች ተናገሩ። መቀመጫውን በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ያደረገው ሳፋሪኮም ኩባንያ፤ እስከ መጋቢት ወር ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ካገኘው 3 ቢሊዮን ዶላር የአገልግሎት ገቢ 10 በመቶ ገደማ የሚሆነው የኢትዮጵያ ገበያ ድርሻ እንደሆነ አስታውቋል።
ኩባንያው የሚመራበት በጀት ዓመት መጠናቀቁን በማስመልከት ባለፈው ሐሙስ ይፋ የተደረገ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ገቢ ባለፈው ዓመት 2.7 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን ዘንድሮ 7.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል። የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ270 ፐርሰንት እድገት ቢያሳይም፤ 47 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኪሳራ እንደገጠመው ዋና ስራ አስፈጻሚው ዊም ቫንሔለንፑት ገልጸዋል።
“ይህ ኪሳራ በአብዛኛው ኩባንያው በሚገኝበት ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ ከምንጠብቀው ጋር የተስማማ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ተግባራዊ ያደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ለውጥ በኩባንያው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ጠቁመዋል። ይህ ለውጥ ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የውጪ ሀገራት መገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለውን ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን አዳክሞታል።

የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ለውጡ፤ በአጭር እና መካከለኛ ጊዜ የሚያሳድራቸውን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም “እርምጃዎች መወሰዳቸውን” የሳፋሪኮም ኃላፊዎች አብራርተዋል። እርምጃው በውጭ ምንዛሬ ክፍያ የሚፈጸምባቸው ውሎችን እንደገና መደራደር እና በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተቀጠሩ የውጪ ሀገር ዜጎችን መቀነስን የካተተ እንደሆነ የሳፋሪኮም ኩባንያ የፋይናንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዲሊፕ ፓል አስረድተዋል።
ቤልጂየማዊው ዊም ቫንሔለንፑት በዋና ስራ አስፈጻሚነት የሚመሩት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 898 ሠራተኞች አሉት። ከእነዚህ መካከል 95 በመቶው ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የቀሩት የውጪ ሀገራት ዜጎች እንደሆኑ የኩባንያው መግለጫ ያሳያል። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ለውጡ የደረሰበትን ተጽዕኖ ለመቋቋም ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል፤ በድምጽ እና በዳታ አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አንዱ መሆኑን የእናት ኩባንያው የፋይናንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለቴሌኮም አገልግሎት ደንበኞች የሚከፍሉት “በጣም ዝቅተኛ” እንደሆነ የተናገሩት ዲሊፕ ፓል፤ “የኢንዱስትሪው የዋጋ ጭማሪ ወደፊት የሚጠበቅ ነገር ነው ብለን እናምናለን” ሲሉ ተደምጠዋል። የዋጋ ጭማሪው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያን የቢዝነስ የስራ አፈጻጸም ቀጣይነት ለማረጋገጥ፤ “ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም” እምነታቸውን ገልጸዋል።

ከተመሰረተ 28 ዓመታት ገደማ ያስቆጠረውን የሳፋሪኮም ኩባንያ የሚመሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ካለው ዕድሜው አንጻር “በህጻን” የሚመሰል እንደሆነ ከትላንት በስቲያ አርብ በናይሮቢ ከተማ በተካሄደ መርሃ ግብር ላይ ጠቁመዋል። በነሐሴ 2014 በድሬዳዋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ አሁንም በኢንቨስትመንት ምዕራፍ ላይ የሚገኝ እንደሆነ ኃላፊዎቹ አስታውሰዋል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ገና ወደ አትራፊነት ባይሸጋገርም፤ የኩባንያው ኃላፊዎች ግን ባለፈው አንድ አመት ባዩት ዕድገት ተነቃቅተዋል። የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የደንበኞች ቁጥር 8.8 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ከነበረበት በእጥፍ ጭማሪ አሳይቷል። “ኤምፔሳ” የተሰኘው የኩባንያውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች ብዛት 2.4 ሚሊዮን መድረሱንም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አስታውቋል።
የነዳጅ ግብይትን ጨምሮ ለአገልግሎቶች ክፍያ ለመፈጸም በሚያስችለው “ኤምፔሳ”፤ ባለፈው አንድ ዓመት 15.8 ቢሊዮን ብር እንደተዘዋወረ ኩባንያው ገልጿል። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ“ኤምፔሳ” የሚሰጥ የብድር እና ቁጠባ አገልግሎት እንደሚጀምርም ይፋ አድርጓል። በኬንያ ይበልጥ ስኬታማ የሆነው “ኤምፔሳ”ን በኢትዮጵያ ለመጀመር የሚያስፈልገውን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ለማግኘት፤ ሳፋሪኮም 150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል።

ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የወጣውን ጨረታ ባሸነፈበት ወቅት ለፈቃድ 850 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉ የሚታወስ ነው። የሳፋሪኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፒተር ን’ዴግዋ፤ የኬንያው ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ “ያልተነካ ገበያ” ስራውን ማስፋፋቱ “የደፋር ውሳኔ” እንደነበር ጠቅሰዋል። በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ “ጠንካራ የንግድ አፈጻጸም ደስተኞች ነን” ያሉት ፒተር፤ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ባለው የቴሌኮም ሽፋን 50 በመቶ የሀገሪቱን ህዝብ መድረስ መቻሉን አብራርተዋል።
ከመንግስታዊው ኢትዮ ቴሌኮም ሌላ ሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅራቢ የሆነው ሳፋሪኮም፤ የቴሌኮም ሽፋኑን ለማድረስ በኢትዮጵያ የሚጠቀምባቸው ማማዎች በኬንያ ካሉት በግማሽ ያነሰ ነው። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 3,141 የቴሌኮም ማማዎችን የሚጠቀም ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 1,718 የሚሆኑትን በኩባንያው የተገነቡ ናቸው። ቀሪዎቹ 1,423 የቴሌኮም ማማዎች ኩባንያው በኪራይ የሚጠቀምባቸው ናቸው።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያን ተደራሽነት እና የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማስፋፋት፤ “ሰፊ የዕድገት ዕድል” እንዳለ የእናት ኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ እምነት አላቸው። ዋና ስራ አስፈጻሚው ፒተር ን’ዴግዋ ለዚህ እምነታቸው እንደ አንድ ምክንያት የሚያስቀምጡት፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው ወጣት መሆኑን ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ተግባዊ የሚያደርጋቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፤ ለኩባንያቸው የስራ እንቅስቃሴ “አዎንታዊ ትሩፋት ያመጣሉ” የሚለው የዋና ስራ አስፈጻሚው ሌላው ምክንያት ነው። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያሳየውን የስራ አፈጻጸም ለማስቀጠል፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጦችን፣ የፖለቲካ አካሄዶችን እና በተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት የሚደረጉ ለውጦችን በአግባቡ አስተውሎ መጓዝን እንደሚጠይቅ ፒተር ከትላንት በስቲያ በነበረው መርሃ ግብር ላይ ይፋ ባደረጉት ሪፖርት ላይ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























