በቤርሳቤህ ገብረ
በአማራ ክልል የሚገኙ ዳኞች፤ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት ወይም “አወዛጋቢ በሆኑ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ “በየትኛውም” ማህበራዊ ሚዲያ “ሃሳብ እንዳይሰጡ” የሚከለክል ደንብ ጸደቀ። ደንቡ በክልሉ የሚገኙ ዳኞች “ሀሰተኛ” ማህበራዊ ሚዲያዎችን “እንዳይጠቀሙ”፣ “እንዳይከተሉ” እና “አባል እንዳይሆኑ” ይከለክላል።
የዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎችን የስነ-ምግባር እና የዲሲፕሊን የሚመለከተው ይህ ደንብ የጸደቀው ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ግንቦት 5፤ 2017 ነው። ደንቡን ያጸደቀው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች አስተዳደር አብይ ጉባኤ፤ ደንቡ ከዚሁ ዕለት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ አስተላልፏል።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች አስተዳደር ጉባኤን ለማሻሻል በ2014 የወጣው አዋጅ፤ ለዳኞች እና ለጉባኤ ተሿሚዎች የስነ ምግባር እና የዲሲፒሊን ደንብ የማውጣት ስልጣን የሰጠው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር ላለው አብይ ጉባኤ ነው። እስካሁን በስራ ላይ የቆየው የስነ ምግባር እና የዲሲፒሊን ደንብ የወጣው በ2007 ዓ.ም ነበር።

ይህ ደንብ “በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ቢሆንም ግልጽነት የጎደላቸው ጉዳዮችን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ” በአዲስ መልክ እንዲዘጋጅ መደረጉን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትላንትናው ዕለት ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የቀድሞው ደንብ የስነ ምግባር መርሆዎችን በውስጡ ቢይዝም፤ “በዝርዝር በማስቀመጥ ረገድ ውስንነት የታየበት” እንደነበር ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ደንቡ “የዲሲፕሊን ጥፋት ደረጃዎችን በማስቀመጥ ረገድ ግልጽነት የሚያንሳቸውን ድንጋጌዎችን” የያዘ እንደነበርም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መረጃ ያመለክታል። አዲሱ ደንብ እንዲዘጋጅ ከተደረገባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ የዲሲፕሊን ክስ የቀረበበትን ዳኛ ወይም የጉባኤ ተሿሚ “መሰረታዊ መብቶችን ለማክበር እና ለማስከበር” የሚያስችሉ “ዝርዝር የአሰራር ስርዓቶችን መደንገግ” በማስፈለጉ እንደሆነ ተጠቅሷል።
በቀድሞው ደንብ ያልነበሩ “የዳኞች ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም” እንዲሁም የቅሬታ እና አቤቱታ አቀራረብን የተመለከቱ ጉዳዮችን ለማካተት አዲሱ ደንብ መዘጋጀቱንም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ገልጿል። በአማራ ክልል ባሉ ፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሲቃኝ “ሁለት ገጽታ ያለው” እንደሆነ በፍርድ ቤቱ መረጃ ላይ ተጠቅሷል።

በርካታ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች፤ የማህበራዊ ሚዲያን “ለበጎ ተግባር” እንደሚጠቀሙበት የጠቆመው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፤ ሆኖም ጥቂቶች ሙያው ከሚጠይቀው ስነ ምግባር ተቃራኒ በሆኑ ድርጊቶች ውስጥ ሲሳተፉ እና ሙያውን እና የፍርድ ቤቶችን ክብር ዝቅ ሲያደርጉ ማስተዋሉን ገልጿል። “የጥቂት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሲቃኝ፤ የዳኝነት ነጻነትን የሚጋፋ፣ ገለልተኝነትን ሳይሆን ወገንተኝነትን የሚያሳይ፣ ማህበረሰቡ ለዳኞች እና ለፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን እምነት፣ ክብርና እና ግምት ዝቅ እንዲል የሚያደርግ መሆኑን እንረዳለን” ሲል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መረጃ አትቷል።
“ስለሆነም የእዚህ አይነት ግብረ ገብነት የጎደላቸውን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞችን የሚከለክሉ ድንጋጌዎች በዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የስነ ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንብ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ሲልም ፍርድ ቤቱ አክሏል። አዲሱ ደንብ የማህበራዊ ሚዲያ አይነቶችን ዝርዝር እና የእነዚህ መድረኮች አጠቃቀም ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ትርጓሜውን አስቀምጧል።
ደንቡ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ረገድ ለዳኞች እና ለጉባኤ ተሿሚዎች የተፈቀዱ ጉዳዮች እና ክልከላዎችንም ዘርዝሯል። ከክልከላዎቹ መካከል “ዳኞች በፖለቲካ፣ በሃይማኖት ወይም አወዛጋቢ በሆኑ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በየትኛውም ማህበራዊ ሚዲያ ሃሳብ መስጠት አይችሉም” የሚለው ይገኝበታል።

ዳኞች “የፖለቲካ ፓርቲ ተመራጭን፣ የፖለቲካ ፉክክሮችን ወይም የፖለቲካ አስተሳሰቦችን” “በመደገፍ ወይም በመቃወም” በማህበራዊ ሚዲያ መግለጽ የተከለከለ መሆኑም በደንቡ ላይ ተደንግጓል። አንድ ዳኛ ግላዊ መረጃውን፣ የራሱን ደህንነት እና ገለልተኛነቱን “አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ” “ከመግለጽ መቆጠብ ያለበት” ስለመሆኑ በስነ ምግባር ደንቡ ላይ ሰፍሯል።
በአማራ ክልል ያሉ ዳኞች፤ ማህበራዊ ሚዲያን “ሌሎችን ሊያስቆጡ የሚችሉ”፣ “ጸብ አጫሪ” ወይም “ክብረ ነክ በሆነ መንገድ” እንዳይጠቀሙ ይኸው ደንብ ያዝዛል። ዳኞች ማህበራዊ ሚዲያ በሚጠቀሙበት ወቅት፤ “የሰዎችን ክብር በጠበቀ”፣ “ሙያን ባከበረ” እና “በቁጥብነት” መሆን እንዳለበትም በደንቡ ላይ ተቀምጧል።
ደንቡ “የሚያስተዳድሯቸው አካላት የማይታወቁ” እና “በድብቅ የሚሰሩ” በሚል የገለጻቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ቡድኖች እና ግለሰቦች ጋር ዳኞች “ግንኙነት እንዳይፈጥሩ” ይከለክላል። ዳኞች በዚህ መልክ በተቋቋሙ ማህበራዊ ሚዲያዎች እና ቡድኖችም “አባል” እንዳይሆኑም በደንቡ ክልከላ ተጥሎባቸዋል። ደንቡ “ሀሰተኛ” ያላቸውን ማህበራዊ ሚዲያዎችን “መጠቀም”፣ “መከተል” አሊያም “አባል መሆንም” ለዳኞች እንደተከለከለ ተገልጿል።

በአማራ ክልል የሚገኙ ዳኞች “ገለልተኝነታቸው ላይ ጥርጣሬ ሊፈጥር በሚችል መልኩ”፤ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን “በጓደኝነት መወዳጀት”፣ “ገጻቸውን መከተል” ወይም “በሌላ በማንኛውም መንገድ” በማህበራዊ ሚዲያ “መቆራኘት” እንደማይችሉ አዲሱ ደንቡ ይደነግጋል። የክልሉ ዳኞች የአንድን ተቋም ምርት ወይም አገልግሎት የሚያስተዋውቁ ተግባራትን መፈጸም እንደማይችሉም በዚሁ ደንብ ተደንግጓል።
ሌላው ለዳኞች በደንቡ ክልከላ የተደረገበት ጉዳይ “የፍርድ ቤትን ክብር እና ተአማኒነት የሚጎዱ” ማህበራዊ ሚዲያዎችን “መጠቀም፣ መከተል እና አባል መሆን” ነው። የዳኞችን እና በየደረጃዉ ያሉ አመራሮችን “ስብዕና እና ክብር የሚያጎድፉ” ማህበራዊ ሚዲያዎችን “መጠቀም፣ መከተል እና አባል መሆንም” በደንቡ በተመሳሳይ ተከልክሏል።
ዳኞች በማህበራዊ ሚዲያ ያጋሩት የጻፉት ወይም በማንኛውም መንገድ የገለጹት ሃሳብ፤ “የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃም የስነ ምግባር ደንብን በጣሰ መልኩ ከሆነ” እንዲያስተካከሉ በተጠየቁ ጊዜ “የማስተካከል ግዴታ” በደንቡ ተጥሎባቸዋል። ደንቡ ማህበራዊ ሚዲያ የሚላቸው በሰዎች መካከል “መረጃ ለመለዋወጥ፣ ይዘቶችን ለመጋራት፣ ለመፍጠር እና ለመተባበር” የሚያስችሉ እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ፣ ሊንክድኢንን የመሰሉ በበይነ መረብ የሚገኙ መድረኮችን ወይም አፕልኬሽኖችን ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)