የህወሓት ቡድን በዛሬው ዕለት የአፋር ክልል ወሰንን ተሻግሮ በመግባት ስድስት መንደሮችን “በጉልበት ተቆጣጥሯል” ሲል የክልሉ መንግስት ወነጀለ። የአፋር ክልል መንግስት ምሽቱን ባወጣው መግለጫ የህወሓት ቡድን ከድርጊቱ “በአስቸኳይ ካልተቆጠበ”፤ ራሱን “ከውጫዊ ጥቃት” የመከላከል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስጠንቅቋል።
የአፋር ክልል መንግስት ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው፤ ዛሬ ምሽት አምስት ሰዓት ገደማ በክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አማካኝነት ባወጣው አጭር መግለጫ ነው። ክልሉ በዚሁ መግለጫው “ጠብ ጫሪ” እና “ከጥፋቱ የማይማረው” ሲል የጠራው የህወሓት ቡድን፤ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 26፤ 2018 ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ በአፋር አርብቶ አደሮች ላይ “የከባድ መሳሪያ” ተኩስ መክፈቱን አስታውቋል።
በሞርታር እና በዙ-23 “ድብደባ” ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት አካባቢዎች በአፋር ክልል፣ ዞን ሁለት፣ መጋሌ ወረዳ፣ ቶንሳ ቀበሌ የሚገኙ አካባቢዎች መሆናቸውንም ክልሉ ገልጿል። የህወሓት ቡድን የአፋር ክልል ወሰንን ተሻግሮ ጥቃት ፈጽሞባቸዋል የተባሉት አካባቢዎች፤ ዋራዓ እና ሚልኪ የሚል መጠሪያ ያላቸው ናቸው።

“የህወሓት ጣብ-ጫሪ ቡድን በቶንሳ ቀበሌ ላይ ተኩስ በሚከፈትበት ወቅት ሰላም ወዳድ የአፋር ሽማግሌዎች እንዲመለሱ ቢማጸኗቸውም፤ ጉጅሌው ግን አሻፈረኝ በማለት ግጭቱን አስከትሏል” ሲል የአፋር ክልል በዚሁ መግለጫው ላይ ወንጅሏል። የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ባደረጉት ንግግር፤ “በከሃዲነት” እና “በወንጀለኛነት” የፈረጁትን የህወሓት ቡድን “ጉጅሌ” የሚል ስያሜ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።
ኤታማዦር ሹሙ በዚሁ ንግግራቸው ህወሓት ከፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት በኋላ አድርጓቸዋል ያሏቸው “ትንኮሳዎች”፣ “እምቢ ባይነቶች”፣ “ስራዎች” እና “ሴራዎች”፤ “ወደ ጦርነት ለመግባት ከበቂ በላይ ናቸው” ሲሉም ተደምጠው ነበር። የአፋር ክልል በምሽቱ መግለጫው፤ “የአዛውንቶች” ስብስብ ያለው የህወሓት ቡድን “በንጹሃን” ላይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በመክፈት “የፕሪቶሪያ ስምምነትን በግጭት አዋጅ በግልጽ አፍርሷል” ብሏል።
በጥቅምት 23፤ 2015 በደቡብ አፍሪካዊቷ ፕሪቶሪያ ከተማ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት ተወካዮች መካከል የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት፤ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት ሲካሄድ የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቋጭ ያደረገ ነበር። የዚሁ ስምምነት መታሰቢያ ሶስተኛ ዓመት በማስመልከት የአውሮፓ ህብረት፣ የህብረቱ አባል ሀገራት እና ኖርዌይ ባለፈው እሁድ ባወጡት መግለጫ፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚዎች መካከል “ፖለቲካዊ ውይይት” ከመጪው ምርጫ በፊት “መልሶ እንዲጀመር” ጥሪ አቅርበው ነበር።
ይህ ጥሪ ከቀረበ ከሁለት ቀናት በኋላ መግለጫ ያወጣው የአፋር ክልል፤ የህወሓት ቡድኑ የክልሉን ወሰን ተሻግሮ ከፈጸመው ድርጊት “በአስቸኳይ እንዲቆጠብ” አሳስቧል። ቡድኑ ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን የአፋር ክልል መንግስት “የዜጎች ደህንነትና የወሰኑን ክብር የማስጠበቅ”፣ እንዲሁም ራሱን “ከማንኛውም ውጫዊ ጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ” ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ከዚህ ማስጠንቀቂያ አንድ ሰዓት ገደማ አስቀድሞ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተሰራጨው የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የአቶ ጌታቸው ረዳ መልዕክት፤ በአፋር ክልል እየተካሄደ ያለው “የፌደራል መንግስትን ወደ ግጭት ለማስገባት” የሚደረግ ሙከራ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ጌታቸው ለዚህ ድርጊት ተጠያቂ ያደረጉት፤ በመልዕክታቸው “ኋላ ቀር” ሲሉ የጠሩትን ቡድን ነው።
የቀድሞው የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር፤ “የሻዕቢያ አጀንዳ” ያሉትን ድርጊት በመፈጸም በቀንደኛነት የወነጀሏቸው ሜጀር ጄነራል ፍስሃ ኪዳኑ (ፍስሃ ማንጁስ) እና ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስን (መዲድ) ነው። አቶ ጌታቸው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነታቸው ከመነሳታቸው አስቀድሞ ከስራ ካገዷቸው ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ውስጥ ሁለቱ የጦር መኮንኖች ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]































