የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ንብረቶቻቸውን  “ያለ ፈቃድ” እንዳያስተላልፉ እና እንዳይሸጡ ተከለከሉ   

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያለ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት “ግልጽ ፈቃድ”፤ የሚንቀሳቀሱም ሆነ የማንይንቀሳቀሱ ንብረቶቻቸውን “እንዳያስተላልፉ”፣ “እንዳያስወግዱ” ወይም “እንዳይሸጡ” ተከለከሉ። ክልከላውን የጣለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፤ ትዕዛዙን ተላልፈው በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ላይ “ተገቢውን እርምጃ” እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ባለስልጣኑ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው፤ ትላንት ማክሰኞ ጥር 26፤ 2018 ዓ.ም. በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው “ጥብቅ ማሳሰቢያ” ነው። በ2011 ዓ.ም. በተሻሻለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፤ ድርጅቶቹ ከየትኛውም ሕጋዊ ምንጭ ሀብት እና ንብረት በማሰባሰብ በህጋዊ እና ሞራላዊ ዓላማዎች ላይ ተሰማርተው መስራት እንደሚችሉ ይደነግጋል።   

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሰረት ስራቸውን ማከናወናቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ባለስልጣኑ፤ “በህዝብ ስም የሚሰበሰቡ” ሀብትና ንብረቶችን “ለህዝብ ጥቅም መዋላቸውን” የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል። ባለስልጣኑ ሁኔታዎችን በማጥናት እና ተጽዕኖቻቸውን በመተንተን፤ ለድርጅቶቹ ድጋፍ እና ቁጥጥርም ያደርጋል። 

እነዚህን ኃላፊነቶቹን መሰረት በማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ንብረት “የማጣራት” እና “የመመዝገብ” ስራ እያከናወነ መሆኑን መስሪያ ቤቱ ገልጿል። ባለስልጣኑ በስም የዘረዘራቸውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ጥሪ ያደረገው ባለፈው ጥቅምት እና ታኅሣሥ ወራት ነበር።

ድርጅቶቹ እንዲሞሉ በወጣው ቅጽ፤ የሰው ሀብት ብዛት፣ ቋሚ ንብረት፣ ተሽከርካሪ እና ሞተር ሳይክል እንዲሁም የቤት እና የቢሮ ዕቃዎችን በዝርዝር እንዲያስመዝግቡ ያዛዝል። በዘርፉ እንደ ሀገር ምን ያህል ንብረት እንዳለ የሚገልጽ ጥቅል መረጃ አለመኖሩን በወቅቱ የገለጸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ የንብረት ምዝገባው ይህንን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ባለስልጣኑ በትላንቱ ማሳሳቢያው የንብረት ማጣራት እና የመመዝገብ ስራው አሁንም እየተከናወነ በመሆኑ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ንብረት ከማስተላለፍ፣ ከማስወገድ እና ከመሸጥ እንዲታቀቡ እገዳ ጥሏል። ሆኖም ክልከላው እስከ መቼ እንደሚቆይ መስሪያ ቤቱ ቀነ ገደብ አላስቀመጠም። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ይህን መሰል ክልከላ ሲያደርግ የመጀመሪያው አይደለም። መስሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ባወጣው “አስቸኳይ መግለጫ”፤ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ ድርጅቶች ያለ መስሪያ ቤቱ “ግልጽ ፍቃድ”፤ ንብረት የማስተላለፍ፣ የማስወገድ እና የመሸጥ ድርጊቶችን እንዳያከናውኑ ከልክሎ ነበር። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ከመደበኛ ወይም ፕሮጀክት ስራዎቻቸው ጋር ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ውጭ፤ ሃብት እና ገንዘባቸውን “በማናቸውም መልኩ” ለሶስተኛ ወገን እንዳያስተላለፉም በወቅቱ እገዳ ጥሎ ነበር። ባለስልጣኑ የሰጠውን ይህን “ጥብቅ ማሳሰቢያ” በመተላለፍ በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ላይ “ተገቢውን እርምጃ” እንደሚወስድም አስጠንቅቆ ነበር። ተቋሙ በትላንቱ ተመሳሳይ ማሳሰቢያውም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)