የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በፓርላማ ሊሾሙ ነው። የኮርፖሬሽኑ ቦርድ አባል እንዲሆኑ ከታጩት ዘጠኝ ግለሰቦች ውስጥ ስድስቱ አዳዲስ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም በ2015 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ፤ የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ ይደነግጋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ሐሙስ ጥር 28፤ 2018 በሚያካሄደው መደበኛ ስብሰባው ለኮርፖሬሽኑ ቦርድ አባልነት በዕጩነት የቀረቡለትን ግለሰቦች መርምሮ ለማጽደቅ አጀንዳ ይዟል።
የኮርፖሬሽኑ ቦርድ፤ የብሔራዊ ቴሌቪዥን እና ሬድዮ ጣቢያዎችን በስሩ የሚያስተዳድረውን ኢቢሲን በበላይነት የሚመራ አካል ነው። ቦርዱ የመገናኛ ብዙሃንን የሚመለከቱ የመንግስት ፖሊሲዎች እና ህጎች በኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት በአዋጅ ተጥሎበታል።

በህዝብ መታወቅ ያለባቸው የመንግስት ፖሊሲዎች እና ህጎች በወቅቱ መተላለፋቸውን ማረጋገጥ ሌላው የቦርዱ ኃላፊነት ነው። በኢቢሲ የሚሰራጩ ፕሮግራሞች ሀገራዊ አንድነትን እና ብልጽግናን ማረጋገጥ ላይ ግብ ያደረጉ መሆናቸውን መከታተልም የተቋሙ ቦርድ ተግባር እንደሆነ በተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሰፍሯል።
የተቋሙ ቦርድ በኮርፖሬሽኑ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን “ሚዲየሞች” የሃሳብ እና የይዘት ብዝሃነት ያላቸው ፕሮግራሞች ተቀርጸው ለህዝብ መቅረባቸው የመከታተል ኃላፊነትም አለበት። የኮርፖሬሽኑ የቦርድ አባላት ቁጥር ከሰባት ማነስ እንደሌለበት የሚያዝዘው የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ግለሰቦቹ አግባብነት ካላቸው ተቋማትና ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እንዲሁም የጾታ ስብጥርን ያማከሉ መሆን እንዳለባቸውም ይደነግጋል።
በነገው የፓርላማ መደበኛ ሹመታቸው እንደሚጸድቅላቸው ከሚጠበቁት የቦርድ አባላት ውስጥ ስድስቱ ለቦታው አዲስ ናቸው። ከአዳዲሶቹ የቦርድ አባላት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ይገኙበታል።

ዲያቆን ዳንኤል ዘጠኝ አባላት የሚይዘውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቦርድን በሰብሳቢነት እንዲመሩ ነው በዕጩነት የቀረቡት። ለመሰል ኃላፊነት እንግዳ ያልሆኑት ዲያቆን ዳንኤል፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባልነትን ሹመት ለሶስት ተከታታይ ጊዜያት አግኝተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬስ ድርጅት ቦርድ አባልነት ለሹመት ሲቀርቡ፤ በዕለቱ የፓርላማ ስብሰባውን ከታደሙ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል 129 ያህሉ የተቃውሞ ድምጻቸውን አስመዝግበው ነበር። አከራካሪው የዲያቆን ዳንኤል ሹመት በወቅቱ የጸደቀው፤ በ146 የፓርላማ አባላት ድጋፍ እና በ27 ድምጸ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ እንደነበር ይታወሳል።
የእዚሁ ተቋም ቦርድ አባላት ሹመት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በፓርላማ በጸደቀበት ወቅት፤ ዲያቆን ዳንኤል ያለምንም ተቃውሞ ለሶስተኛ ጊዜ የኃላፊነታቸውን ቦታ አስጠብቀዋል። በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ በግል ተወዳድረው የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል፤ ለአራተኛ ጊዜ ለሹመት ፓርላማ የሚቀርቡት ከእርሳቸው በፊት የኢቢሲ ቦርድን በሰብሳቢነት ይመሩ የነበሩትን ዶ/ር ለገሰ ቱሉን ለመተካት ነው።

ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትርነታቸው ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ የተነሱት ዶ/ር ለገሰ፤ ከወር በኋላ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ተመድበዋል። ዶ/ር ለገሰ ለሶስት ዓመታት በሰብሳቢነት የመሩትን የኢቢሲ ቦርድ፤ የቀድሞው መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ እና አቶ አህመድ ሽዴም እንዲሁ በተለያዩ ጊዜያት ተሹመውበት ነበር።
በነገው እለት ሹመታቸው እንደሚጸድቅላቸው ከሚጠበቁት የኢቢሲ አዳዲስ የቦርድ አባላት መካከል የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ወርቁ ጋቸና ይገኙበታል። የሰላም እና የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዎቹ አቶ ቸሩ ጌታ ገነነ እና ዶ/ር እንደገና አበበ እንዲሁ በአዲስ የቦርድ አባልነት በዕጩነት ቀርበዋል።
ቀድሞውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ፤ ለኢቢሲ የስራ አመራር ቦርድ አባልነት የታጩት ሌላኛው አዲስ ተሿሚ ናቸው። ዶ/ር ጌታቸው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል በማስተማር ላይ ይገኛሉ።

በተቋሙ የቦርድ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካኝነት ስም ዝርዝራቸው ለፓርላማ ከተላኩ ግለሰቦች መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር አባል የሆኑት አቶ የሱፍ ኢብራሂም ይገኙበታል። አቶ የሱፍ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ።
እንደ አቶ ዩሱፍ ሁሉ የብልጽግና ፓርቲ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊው ዶ/ር አብዱልዋሳ አብዱላሂ በኢቢሲ ቦርድ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ በድጋሚ ለሹመት ቀርበዋል። የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ጃፋር በድሩም በኢቢሲ እንዲሁ ለሁለተኛ ጊዜ የተቋሙ የቦርድ አባል እንዲሆኑ ስማቸው ለፓርላማ ተላልፏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































![“ኢትዮጵያ በህዳሴ [ግድብ] ላይ አንድም ብር እርዳታ፤ አንድም ብር ብድር አልወሰደችም” – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ](https://ethiopiainsider.com/wp-content/uploads/2026/01/Grand-Ethiopian-Renaissance-Dam-GERD-in-September-2025-Office-of-the-Prime-Minister-of-Ethiopia-218x150.jpeg)