የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤፍ ኤም) የስራ አስፈጻሚ ቦርድ፤ ለኢትዮጵያ መንግስት 464 ሚሊዮን ዶላር ብድር “ወዲያውኑ እንዲለቀቅ” የሚያስችል ውሳኔ አሳለፈ። የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ውሳኔውን ያሳለፈው፤ የኢትዮጵያን የተራዘመ ብድር አቅርቦት (ECF) አምስተኛ ዙር ግምግማን ከተመለከተ በኋላ ነው።
የአይ ኤም ኤፍ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ለአራት ዓመታት የሚቆየውን የኢትዮጵያን የተራዘመ የብድር አቅርቦት ያጸደቀው በሐምሌ 2016 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የሚያደርጋቸውን ግምገማዎች መሰረት በማድረግ፤ ከዚህ ቀደም ለአራት ጊዜያት ያህል የተለያየ መጠን ያላቸውን ብድሮች ለኢትዮጵያ መንግስት ሲለቀቅ ቆይቷል።
የድርጅቱ የባለሙያዎች ቡድን አምስተኛ ዙር ግምገማ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ነበር። ከቡድኑ ጉብኝት በኋላ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት “በባለሙያዎች ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸው” ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ይፋ ተደርጓል።
አይ ኤም ኤፍ በዚሁ ወቅት ባወጣው መግለጫ፤ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ 468 ሚሊዮን ዶላር ብድር መልቀቅ የሚያስችል እንደሆነ ገልጾ ነበር። ድርጅቱ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 24፤ 2018 ለሊት ባወጣው መግለጫ ይፋ ያደረገው የብድር መጠን ግን ባለፈው ግንቦት ወር ከተገለጸው በአራት ሚሊዮን ዶላር ያነሰ ነው።
ኢትዮጵያ ያለባትን “የክፍያ ሚዛን” ጉድለት እና “የበጀት ፋይናንስ ፍላጎቶቿን” እንድታሟላ ያግዛታል የተባለለት ይህ ብድር፤ አይ ኤም ኤፍ በ48 ወራት ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ መንግስት ለማበደር የተስማማው 3.4 ቢሊዮን ዶላር አካል ነው። የአሁኑ ብድር ሲለቀቅ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተበደረችውን አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ከ2.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያደርሰዋል።
አጠቃላይ የብድር ስምምነቱ፤ በገበያ ወደሚወሰን የውጪ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት መሸጋገርን ጨምሮ ኢትዮጵያ አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦችን እንድታደርግ ያስገድዳታል። የብድር መርሃ ግብሩ አጠቃላይ አፈጻጸም፤ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ከገባቻቸው ማሻሻያዎች ጋር “የተጣጣመ” እንደሆነ አይ ኤም ኤፍ በዛሬው መግለጫው አመልክቷል።

የአይ ኤም ኤፍ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ናይጄል ክላርክ፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሀገሪቱ ባለስልጣናት “መሻሻሎች ማሳየታቸውን” መናገራቸውን በዛሬው የድርጅቱ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። የሀገሪቱን “የማክሮ ኢኮኖሚ ግስጋሴ” ለማስቀጠል፤ ቀጣይነት ያላቸው የማሻሻያ ጥረቶች እና በየጊዜው ለሚፈጠሩ ተግዳሮቶች የሚሰጡ “ብልህ ምላሾች” አስፈላጊ እንደሆኑም የቦርድ ሰብሳቢው አስገንዝበዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጭምር የሆኑት ናይጄል ክላርክ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገባቸውን ጉዳዮችም አንስተዋል። የውጭ ምንዛሬ ገበያ፣ የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋት፣ የወጪ አስተዳደር፣ ዘላቂነት ያለው የገቢ ማሰባሰብ፣ የሀገሪቱ ዕዳ ሽግሽግ እና የፋይናንስ ዘርፍ ቁጥጥር በቦርድ ሰብሳቢው የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።
“የሚጠበቁ የዋጋ ግሽበቶች ለማረጋጋት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋምን ጠብቆ መቀጠል አሁንም ተገቢ ነው” ያሉት ክላርክ፤ በሀገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ጫናዎች የሚከሰቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ መቆጣጠሪያውን “የበለጠ ለማጥበቅ” ዝግጁ መሆን እንደሚገባው ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት ባለፈው ሚያዝያ ወር 11.7 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ስታቲክስ አገልግሎት አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]
































